ሃማስ ትጥቅ ለመፍታት ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
የሃማስ ከፍተኛ የፖለቲካ መሪ ቡድኑ ከእስራኤል ጋር ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ ብለዋል
እስራኤል ግን ሃማስን መደምሰስ ብቸኛው አማራጭ ነው በሚል በራፋህ ጦርነት ለመጀመር እየተዘጋጀች ነው
ሃማስ ትጥቅ በመፍታት ሙሉ በሙሉ ወደ ፖለቲካ ድርጅትነት ለመለወጥ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።
የቡድኑ ከፍተኛ የፖለቲካ መሪ ካሊል አል ሃያ ከአሶሼትድ ፕረስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሃማስ ከእስራኤል ጋር ለአምስት አመት ወይም ከዚያም በላይ የሚዘልቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የፍልስጤሙ ቡድን ከእስራኤል ጋር ባካሄዳቸው የተኩስ አቁምና የእስረኞች ልውውጥ ተሳታፊ የነበሩት አል ሃያ፥ ሃማስ ዌስትባንክን ከሚያስተዳድረው ፋታህ ጋር በመዋሃድ ጋዛና ዌስትባንክን የሚያስተዳድር የአንድነት መንግስት ለማቋቋም ፍላጎት እንዳለውም አንስተዋል።
ይህ እንዲሆን ግን ነጻዋ ፍልስጤም መመስረትና የ”ሁለት መንግስታት መፍትሄ” ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል ነው ያሉት።
እስራኤል በ1967ቱ የስድስት ቀናት ጦርነት በሃይል የተቆጣጠረቻቸውን አካባቢዎች መልቀቅና ወታደሮቿን ሙሉ በሙሉ ማስወጣት እንደሚኖርባትም አብራርተዋል።
ቴል አቪቭ ይህን ተፈጻሚ ካደረገች የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ ሙሉ በሙሉ እንደሚፈርስም በማከል።
ሃማስን ካልተደመሰሰ ምንም የደህንነት ዋስትና የለኝም የምትለው እስራኤል ግን ይህን የሃማስ ጥያቄ ትቀበለዋለች ተብሎ አይጠበቅም።
የቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር በራሃፍ መሽገዋል ያላቸውን የቡድኑን ታጣቂዎች ለመደምሰስ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑንም ገልጿል።
የሃማስ ከፍተኛ የፖለቲካ መሪው ካሊል አል ሃያ ግን የእስራኤል የጋዛ ዘመቻ ሃማስን እንደማያጠፋው ነው የተናገሩት።
ጦርነቱ ሰባተኛ ወሩን ሊይዝ ቢቃረብም የቡድኑ የፖለቲካና ወታደራዊ ክንፍ ግንኙነቱ እንዳልተበጠሰና እያንዳንዱ ውሳኔና አቅጣጫ በምክክር እንደሚደረግም አንስተዋል።
እስራኤል እስካሁን በፈጸመችው ጥቃት በሃማስ የሰው ሃይልም ሆነ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ 20 በመቶውን እንኳን አለማጥፋቷን በመጥቀስም፥ “ሃማስን ማጥፋት ካልቻሉ ምንድነው መፍትሄው?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
የሃማስ ከፍተኛ የፖለቲካ ቢሮ መሪው መፍትሄው መነጋገር ነው ቢሉም የተኩስ አቁም ድርድሮች የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጡ ሃማስ የሚያቀርባቸው ቅድመሁኔታዎች ለእስራኤል ፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው መሆናቸው በምክንያትነት ይነሳል።
አል ሃያ ግን ሃማስ ታጋቾችን ለመልቀቅ በእስራኤል መፈታት ያለባቸው የፍልስጤማውያን እስረኞች ቁጥርን በተለያየ ጊዜ ዝቅ ማድረጉን ያነሳሉ።
ሃማስ የእስራኤል ወታደሮች ሙሉ በሙሉ ከጋዛ ካልወጡ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት አልፈራረምም የሚለው አቋሙ ግን አሁንም አልተቀየረም ብለዋል።
እስራኤልም ሆነች ዌስትባንክን የሚያስተዳድረው አለማቀፍ እውቅና ያለው የፍልስጤም አስተዳደር ለሃማስ ትጥቅ የመፍታት ሃሳብ ምላሽ አልሰጡም።