የግብጽ ልኡክ ቡድን በተኩስ አቁም እና ታጋቾች ጉዳይ ለመነጋገር እስራኤል መግባቱ ተነገረ
የግብጽ ልኡክ ወደ እስራኤል ያቀናው አሜሪካ እና ሌሎች 17 ሀገራት ሀማስ ሁሉንም ታጋቾች እንዲለቅ ከጠየቁ ከአንድ ቀን በኋላ ነው
የግብጽ የልኡክ ቡድን በትናንትናው እለት ከእስራኤል አቻው ጋር ተገናኝቶ የጋዛ ተኩስ አቁም ንግግር ስለሚጀመርበት ሁኔታ ተወያይቷል
የግብጽ ልኡክ ቡድን በተኩስ አቁም እና ታጋቾች ጉዳይ ለመነጋገር እስራኤል መግባቱ ተነገረ።
የልኡክ ቡድኑ በትናንትናው እለት ከእስራኤል አቻው ጋር ተገናኝቶ የጋዛ ተኩስ አቁም ንግግር ስለሚጀመርበት እና ያልተለቀቁ ታጋቾች ስለሚለቀቁበት ሁኔታ ተወያይቷል።
ሮይተርስ አንድ በስብስባው የተገኙ እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው እስራኤል አዲስ ምክረ ሀሳብ እንደሌላት እና ቀደም ሲል ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ለማድረግ 40 ታጋቾች እንዲለቀቁ የጠየቀችውን ወደ 33 ዝግ አድርጋለች።
ባለስልጣኑ "በአሁኑ ወቅት በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ታጋቾችን የተመለከተ ጉዳይ አልተነሳም፤ በዚህ ረገድ እስራኤል ያቀረበችው አዲስ ሀሳብም የለም" ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
ባለስልጣኑ "አሁን ያለው ግብጽ ባቀረበችው የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ ዙሪያ ንግግር የመጀመር ጥረት ነው" ብለዋል።
በሀማስ እና በፍልስጤም ታጣቂዎች ተይዘው ካሉት 133 ታጋቾች ውስጥ 33 ህጻናት፣ በእድሜ የገፉ እና ህመምተኞች በህይወት መኖራቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙኻን የደህንነት ምንጮችን ጠቅሰው ዘግበዋል።
ይደረገል የተባለው ተኩስ አቁም ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ እንደማይታወቅ እና የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ የሚኖር ከሆነ ግን ተኩስ የሚቆም ከስድስት ሳምንት ላልበለጠ ጊዜ መሆኑን ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
የግብጽ ልኡክ ወደ እስራኤል ያቀናው አሜሪካ እና ሌሎች 17 ሀገራት ሀማስ ሁሉንም ታጋቾች ለቆ ለጋዛው ቀውስ መቆም መንገድ እንደሚያመቻች ከጠየቁ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ሀማስ "የህዝባችንን መብት እና ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገቡ ምክረ ሀሳቦችን ለመቀበል ክፍት" መሆኑን ገልጿል።
ነገርግን ሀማስ በጋዛ ዘላቂ ተኩስ አቁም ማድረግ እና የእስራኤል ጦር ከዛ ለቆ መውጣት ጉዳይ የማይደራደርባቸው መሰረታዊ ቅድመሁኔታዎች ናቸው።
እስራኤል በአንጻሩ የጋዛን የጸጥታ ስራ በዘላቂነት መቆጣጠር ትፈልጋለች።
እስራኤል እና ሀማስ ለማድራደር የተደረገው ጥረትም አንዳቸው ሌላኛቸው ያቀረቡትን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ እያደረጉ በመቀጠላቸው እስካሁን አልተሳካም።
ሀማስ በጥቅምት ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል እየወሰደች ባለው የአየር እና የምድር ጥቃት ከ34ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።