ባይደን ኩባን ሽብርተኝነትን በመንግስት ደረጃ ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ለማስወጣት ወሰኑ
የተሰናባቹን ፕሬዝዳንት ውሳኔ ተከትሎ ሃቫና 553 እስረኞችን እንደምትፈታ አስታውቃለች
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ ኩባን ዳግም ሽብር ፍረጃው በመመለስ ማዕቀቦችን መጣላቸው ይታወሳል
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሽብርተኝነትን በመንግስት ደረጃ ስፖንሰር ታደርጋለች በሚል የተፈረጀችውን ኩባ ከዝርዝሩ ለማስወጣት ወሰኑ።
ኩባን ከሽብር ፍረጃው ለማስወጣት ሃቫና የፖለቲካ እስረኞች እንድትለቅ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን አማካኝነት ድርድር መደረጉን ዋይትሃውስ አስታውቋል።
የተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ውሳኔ እንደተሰማ ኩባ 553 በተለያየ ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ለመፍታት መወሰኗን ገልጻለች።
ከሚለቀቁት እስረኞች ውስጥ ወደ 500 የሚጠጉት በ2021ዱ ህዝባዊ ተቃውሞ የተሳተፉና እስከ 25 አመት እስር የተፈረደባቸው ናቸው ተብሏል።
የመብት ተሟጋቾች እና አሜሪካ ግን ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው የታሰሩ ኩባውያን ቁጥር ከ1 ሺህ እንደሚበልጥ ይገልጻሉ።
የባይደን የመጨረሻ ስአት ውሳኔ ከቀናት በኋላ ዋይትሃውስ በሚገቡት ዶናልድ ትራምፕ እንደሚቀለበስ ይጠበቃል።
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ (2021) ኩባን ዳግም በሽብርተኛ ሀገር ዝርዝር ውስጥ ማስገባታቸውና ሃቫና ከዋሽንግተን የምታገኘው የኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲቋረጥ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የትራምፕ ውሳኔ በደሴቷ የነዳጅ፣ የምግብ፣ መድሃኒት እና ኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረትን አስከትሎ የሀገሪቱን የምጣኔ ሃብት ቀውስ ማባባሱን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
ስማቸው ያልተጠቀሰ የባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን "ያደረግነው ግምገማ ተጠናቋል፤ በዚህም ኩባ በመንግስት ደረጃ ሽብርተኝነትን የምትደግፍ ሃገር መሆኗን የሚያመላክት መረጃ አላገኘንም" ብለዋል።
ባይደን ከነጩ ቤተመንግስት ከመውጣታቸው ከቀናት በፊት ኩባን ከሽብርተኝነት ፍረጃው ዝርዝር ማስወጣታቸውን የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጎ እርምጃ ነው ብሏል።
ኩባ በ2021 ለተቀሰቀሰው ተቃውሞም ሆነ ይህንኑ ተከትሎ ለተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ አሜሪካን ተጠያቂ ታደርጋለች።
ፕሬዝዳንት ሚጉየል ዲያዝ ካነል የአሜሪካን ማዕቀቦች "የዘር ማጥፋት" ሲሉ የገለጹት ሲሆን፥ ትራምፕ ዳግም ወደ ስልጣን ሲመጡ ሊከሰት ለሚችለው ፈታኝ ሁኔታም ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።
ትውልደ ኩባውያን እና በትራምፕ ካቢኔ ውስጥ የተካተቱ ባለስልጣናት የባይደን ውሳኔ ለኩባ ጨቋኝ አገዛዝ እውቅና የሰጠ ነው በሚል እየተቃወሙት ነው።
ሰሜን ኮሪያ፣ ሶሪያ እና ኢራን ሽብርተኝነትን በመንግስት ደረጃ ስፖንሰር ያደርጋሉ በሚል በአሜሪካ በሽብር ፍረጃ ዝርዝር ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል።