ባይደን ከሃኒየህ ግድያ በኋላ ለኔታንያሁ ደውለው መምከራቸውን ገለጹ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የሃማስ የፖለቲካ መሪው መገደል ለተኩስ አቁም ድርድሩ አይጠቅምም ብለዋል
ኢራን በእስራኤል ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ በቀጠናው ከምትደግፋቸው ታጣቂዎች ጋር እየመከረች ነው ተብሏል
የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ መሪው ኢስማኤል ሃኒየህ መገደል የ10 ወራቱን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው የተኩስ አቁም ድርድር ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ትናንት ምሽት ለጋዜጠኖች በሰጡት መግለጫ፥ “የሃኒየህ መገደል ለተኩስ አቁም ድርድሩ ፋይዳ የለውም” ብለዋል።
ባይደን ኢራንን ጨምሮ በርካታ ሀገራትን ባስቆጣው ግድያ ዙሪያ ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ደውለው መነጋገራቸውንም ነው የገለጹት።
ሁሉንም የሃማስ የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች ለመግደል ሲዝት የከረመው የኔታንያሁ አስተዳደር እስካሁን ለሃኒየህ ግድያ ሃላፊነቱን አልወሰደም።
ከ40 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት በተኩስ አቁም ስምምነት እንዲቆም ጥረት ስታደርግ የቆየችው አሜሪካም ከሃኒየህ ግድያ ጋር በተያያዘ የምታውቀው መረጃ እንደሌለ መናገርን መርጣለች።
ኒውዮርክ ታይምስ ግን የእስራኤል የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) የሃኒየህን እንቅስቃሴ ለወራት ሲከታተል ቆይቶ በቴህራን በሚያርፉበት ጥብቅ ክትትል በሚደረግበት አፓርታማ ውስጥ ከርቀት የሚተኮስ ቦምብ ከሁለት ወራት በፊት ማስገባቱን በትናንትናው እለት ዘግቧል።
ይህን የሞሳድ የወራት ክትትልና ሃኒየህን የመግደል ዘመቻ ዋሽንግተን አታውቀውም ማለት አይቻልም የሚሉ ተንታኞች፥ የሃኒየህ ግድያ የኔታንያሁ አስተዳደር የጋዛውን ጦርነት አድማስ የማስፋትና አሜሪካን ጣልቃ የማስገባት አላማ ያለው መሆኑን ያብራራሉ።
በግዛቷ የተፈጸመው ግድያ ሉአላዊነቷን የተዳፈረ መሆኑን ያነሳችው ኢራንም የሃማስ የፖለቲካ መሪውን ኢስማኤል ሃኒየህ ደም እንደምትበቀል መዛቷ የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረትን አባብሶታል።
ቴህራን በቀጠናው የምታስታጥቃቸውን የፍልስጤም፣ የሊባኖስ፣ የመን እና ኢራቅ ታጣቂ ቡድኖች መሪዎች ጠርታም በቴል አቪቭ ላይ በሚወሰደው እርምጃ ዙሪያ ከትናንት ጀምሮ እየመከረች መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል።
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ከእስራኤል ጋር ተኩስ ሲለዋወጥ የከረመው የሊባኖሱ ሄዝቦላህም የእስራኤል ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን እንደሚያደርስ ዝቷል።
የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን መትተው የሚጥሉ እንደ ‘አሮው” እና “አይረን ዶም” ያሉ የአየር መቃወሚያ ስርአቶቿን አዘጋጅታ በተጠንቀቅ እየተጠባበቀች ነው ተብሏል።
የሃማሱ የፖለቲካ ቢሮ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ ስርአተ ቀብር በዛሬው እለት በኳታር ይፈጸማል።