አሜሪካ፤ ታይዋንን ከቻይና ወረራ ለመጠበቅ ኃይል ልትጠቀም እንደምትችል አስታወቀች
ቻይና የኢንዶ-ፓሲፊክ ትብብር አሜሪካ ቀጣናውን ለመከፋፈል በማሰብ የጀመረችው ነው በሚል ተቃውማለች
ታይዋንን ለመጠበቅ ኃይል ልትጠቀም እንደምትችል አሜሪካ አስታወቀች
በእስያ ጉብኝት ላይ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሃገራቸው ታይዋንን ለመጠበቅ ኃይል ልትጠቀም እንደምትችል ተናገሩ፡፡
ባይደን ቻይና ታይዋንን በተመለከተ ኃይል የምትጠቀም ከሆነ እኛም መጠቀማችን አይቀርም ብለዋል፡፡
እንዲህ ዐይነቱ ሁኔታ እምብዛም ሊሆን የሚችል አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ የሚሆን ከሆነ ግን ኃይል እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በቶኪዮ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው ይህን ያሉት፡፡ ይህ ማለት ግን የፖሊሲ ወይም የአቋም ለውጥ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ታይዋን የዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ በቻይና ልወረር እችላለሁ የሚል ስጋት ላይ ወድቃለች፡፡ በተጠንቀቅ ላይ እንደምትገኝም ደጋግማ ገልጻለች፡፡
ይህ ጉዳይ ጃፓንን ጭምር ያሰጋ ነው፡፡ በደቡባዊ ቻይና በሚገኙ ውሃማ አካላት ጉዳይ ከቻይና ጋር የምትወዛገበው ጃፓን አጸፋዊ ምላሾች ለመስጠት በሚያስችል መልኩ ጦሯን እንደምታጠናክር አስታውቃለች፡፡
የ‘ዋን ቻይና’ ፖሊሲን የምትደግፈው አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ የጠራ አቋም የላትም፡፡ በራስ ገዟ ደሴት ኤምባሲም ሆነ ሌላ የግንኙነት ጉዳዮችን የሚያስፈጽም ተቋም የላትም፡፡ ሆኖም ኢ-መደበኛ ግንኙነቶችን ታደርጋለች፡፡ ጦር መሳሪያን ጨምሮ ለታይዋን የተለያዩ ድጋፎችን ታደርጋለች፡፡
ነገር ግን አሜሪካ ጉዳዩ ወደ ጦርነት ጭምር ሊያመራ የሚችል ስለሆነ በተናጠል የምትወስደው እርምጃም ሆነ የምታደርገው ይፋዊ ስምምነት የለም፡፡ ይህን የግንኙነት መንገድም ‘ስትራቴጂክ አምቢጊዩቲ’ ይሉታል በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች፡፡
በደቡብ ኮሪያ የነበራቸውን የሶስት ቀናት ቆይታ አጠናቀው ትናንት እሁድ ጃፓን ቶኪዮ የገቡት ጆ ባይደን ሃገራቸው በእስያ ቀጣና ያላትን ተጽዕኖ ለማጠናከር በሚያስችል የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝት ላይ ናቸው፡፡
በቶኪዮ በሚኖራቸው ቆይታ የህንድ እና የአውስትራሊያ መሪዎችን እንደሚያገኙና የኢንዶ-ፓሲፊክ የትብብር ማዕቀፍ ስብሰባን እንደሚመሩ ይጠበቃል፡፡ የትብብር ማዕቀፉ 13 አዳዲስ ሃገራትን በአባልነት እንደሚያካትት መገለጹ ይታወሳል፡፡
በትብብር ማዕቀፉ ያልተካተተችው ቻይና ማዕቀፉ አሜሪካ ቀጣናውን ለመከፋፈልና ለማቃቃር በማሰብ የጀመረችው እንደሆነ በመግለጽ መቼም እንደማይሳካ አስታውቃለች፡፡