ፕሬዝዳንት ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን ቢያገሉ ማን ሊተካቸው ይችላል?
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባለቤት ሚሼል ኦባማ ፕሬዝዳንት ባይደንን ይተካሉ ከተባሉት መካከል ዋነኛው ሆነዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2024/7/04/258-170131-img-20240704-160108-530_700x400.jpg)
ዲሞክራቶች ዶናልድ ትራምፕን ሊገዳደር የሚችል እጩ ፍለጋ ላይ ናቸው ተብሏል
ፕሬዝዳንት ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን ቢያገሉ ማን ሊተካቸው ይችላል?
የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፓርቲያቸው ዲሞክራት የፊታችን ሕዳር ላይ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እንዲወዳደሩ ዋነኛ እጩ አድርጓቸዋል።
የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ባይደን ባሳለፍነው ሳምንት ከሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ከሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የፊት ለፊት ክርክር አድርገው ነበር።
በዚህ የምርጫ ክርክር ላይ ፕሬዝዳንት ባይደን መናገር ሲያቅታቸው፣ ቃላትን ለማውጣት እና ትኩረታቸውን ለመሰብሰብ ሲቸገሩ ታይተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ የበለጠ ትኩረታቸውን ሰብስበው ሲከራከሩ መታየታቸውን ተከትሎ ዲሞክራቶች መደናገጥ ውስጥ ገብተውም ነበር።
በዚህ ምክንያትም ፕሬዝዳንት ባይደን በምርጫው የማሸነፍ እድል ላይኖራቸው ይችላል በሚል ፓርቲያቸው ተተኪ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህን ተከትሎ ሮይተርስ ዶናልድ ትራምፕን ሊገዳደር የሚችሉ እጩዎች እነማን ሊሆኑ ይችላሉ? ሲል ጥናት አካሂዷል።
በጥናቱ የተሳተፉ አሜሪካዊያን መካከል የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባለቤት ሚሼል ኦባማ የተሻለ ድምጽ አግኝተዋል።
ከሚሼል ኦባማ በመቀጠል የወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ በሁለተኝነት ሲጠቀሱ የካሊፎርኒያው ገዢ ጋቪን ኒውሶም ደግሞ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ሚሼል ኦባማ እስካሁን ፕሬዝዳንት የመሆን ፍላጎት እንዳላት በይፋ ያልገለጸች ሲሆን ፕሬዝዳንት ባይደን ራሳቸውን ከምርጫው ካገለሉ ግን ፓርቲያቸውን ወክለው ሊወዳደሩ ይችላሉ ተብሏል።
የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ባንድ በኩል የቀረቡባቸውን ከ30 በላይ ክሶች በየችሎቱ እየተከራከሩ በሌላ በኩል ደግሞ ዲሞክራቶችን እያስጨነቁ ናቸው።