ፕሬዝዳንት ባይደን የዩክሬንን ጦርነት ለማቆም ከቱፒን ጋር ለመምከር ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ
ከፕሬዝዳንት ፑቱን ጋር በአካል መገናኘት እንደሚፈልጉም ፕሬዝዳንት ባይደን ገልጸዋል
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዋሸንግተንን ጎብኝተዋል
ፕሬዝዳንት ባይደን የዩክሬንን ጦርነት ለማቆም ከሩሲያ አቻቸው ጋር ለመምከር ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከፈረንሳይ አቻቸው ጋር በዋሸንግተን ተገናኝተው መምከራቸው ተገልጿል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ሌሎች ጉዳዮች ደግሞ የሁለቱ ሀገራት ፕሬዝዳንቶች የተወያዩባቸው አጀንዳዎች እንደሆኑ ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ባይደን የዩክሬንን ጦርነት ለማቆም ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመምከር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይሁንና ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦርነቱን ለማቆም ፍላጎት እንዳላሳዩ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ባይደን "ይሄን ጦርነት ለማቆም ብቸኛው መፍትሄ ሩሲያ ጦሯን ከዩክሬን ማስወጣት ብቻ ነው" ሲሉም አክለዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲንን በአካል ማግኘት እፈልጋለሁ የሚሉት ፕሬዝዳንት ባይደን ከፑቲን ጎን ቁጭ ብዬ አዕምሮው ውስጥ ምን እንዳለ እና ምን እንደሚያስብ ማወቅ እፈልጋለሁም ብለዋል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው ዩክሬናዊያን በግዛታቸው እና በሀገራቸው ጉዳይ መወሰን እና መደራደር የሚችሉት ዩክሬናዊያን ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዩክሬን ጉዳይ ግንኙነታቸው ወደ ተባባሰ ሁኔታ የተቀየረው ሩሲያ እና አሜሪካ ባለስልጣናት በያዝነው ሳምንት በኑክሌር ጦር መሳሪያ ቁጥጥር ዙሪያ በግብጽ መዲና ካይሮ ተገናኝተው ለመምከር ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም ሩሲያ በመድረኩ እንደማትሳተፍ አስታውቃለች፡፡
ሩሲያ በዚህ መድረክ ላይ ለመሳተፍ ይዛው የነበረውን ቀጠሮ የሰረዘችው አሜሪካ ጸረ ሩሲያ የሆኑ ስራዎችን ባለማቆሟ እና ይህንን የካይሮ ውይይት መድረክ ለራሷ በሚጠቅም መንገድ ለመፈጸም በማሰቧ እንደሆነ ገልጻለች፡፡
የሁለቱ ሀገራት የደህንነት ሃላፊዎች ከሁለት ሳምንት በፊት በተርኪየ የኢኮኖሚ መዲና ኢስታንቡል ተገናኝተው በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ መምከራቸው ይታወሳል፡፡