የቻይና ኑክሌር ጦር መሳሪያ እድገት እንዳሳሰባት አሜሪካ ገለጸች
ቻይና የአሜሪካንን የጦር መሳሪያ የበላይነት ለመውሰድ በኑክሌር ጦር መሳሪያ ላይ እየሰራች እንደሆነ ተገለጸ
አሁን ላይ 400 የኑክሌር ጦር መሳሪያ ያላት ቻይና ከ10 ዓመት በኋላ ቁጥሩን ወደ 1500 የማሳደግ እቅድ አላት ተብሏል
ቻይና የአሜሪካንን የጦር መሳሪያ የበላይነት ለመውሰድ በኑክሌር ጦር መሳሪያ ላይ እየሰራች እንደሆነ ተገለጸ።
የዓለማችን ቀዳሚ የህዝብ ብዛት ባለቤት የሆነችው ቻይና ወታደራዊ ሪፖርት ይፋ ሆኗል።
በአሜሪካ መከላከያ ይፋ በሆነው ወታደራዊ ሪፖርት መሰረት ቻይና ከ20 ዓመት በፊት ጥቂት የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች እንደነበሯት ተገልጿል።
አሁን ላይ ቻይና 400 የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች አሏት የተባለ ሲሆን ከበፈረንጆቹ 2035 ላይ የዓለማችን ቀዳሚ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ያሏት ሀገር የመሆን እቅድ እንዳላት ሲኤንኤን የፔንታጎን ሀላፊዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ቻይና የአሜሪካንን የጦር መሳሪያ የበላይነት ለመውሰድ እቅድ አላት ያለው ዘገባው የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ብዛት ወደ 1500 ከፍ ለማድረግ እቅድ አላትም ተብሏል።
ቻይና የኑክሌር አረሮችን በባህር ላይ፣ ምድር ላይ፣ በአየር እና በወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች ላይ በየዓመቱ እያወጣች ያለው በጀት እየጨመረች ሲሆን ይህም አሜሪካንን እንዳሳሰበ ተገልጿል።
ቻይና ባለፈው የፈረንጆቹ 2021 ዓመት ብቻ 135 ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ለሙከራ የተኮሰች ሲሆን ይህም ከቤጂንግ ውጪ ያሉ ሌሎች የዓለማችን ሀገራት ከሞከሩት ድምር ይበልጣል ተብሏል።
በተጨማሪም ቻይና በዚህ 2021 ዓመት 400 ኪሎ ሜትር በሰዓት መጓዝ የሚችል የሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤል ሙከራን ማሳካቷን አሜሪካ ገልጻለች።
አንድ ሚሊዮን ወታደሮች እንዳሏት የሚገለጸው ቻይና በባህር ሀይል ከዓለማችን አንደኛ፣ በአየር ሀይል ወታደሮች ደግሞ ሶስተኛ ሀገር እንደሆነች በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።