የፖለቲካ ባላንጣዎቹ አሜሪካ እና ኢራን በዓለም ዋንጫው ዛሬ ይፋለማሉ
በዓለም ዋንጫው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ ሴኔጋል ከኢኳዶር ፤ ዌልስ ከእንግሊዝ የሚያደርጉት ጨዋታም ይጠበቃል
ኢራን በአለም ዋንጫ የተሳትፎ ታሪኳ አሜሪካን በማሸነፍ ነው የመጀመሪያ ድሏን ያስመዘገበችው
የኳታሩ የአለም ዋንጫ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ የጂኦፓለቲካ ተቀናቃኞቹ አሜሪካ እና ኢራን ይጫወታሉ።
አፍሪካን የወከለችው ሴኔጋልም ከኢኳዶር ተጠባቂ ጨዋታ 12 ስአት ላይ ታደርጋለች።
የታራንጋ አንበሶቹ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በካሊፋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የሚያደርጉትን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።
በተመሳሳይ 12 ስአት ኔዘርላንድስ አስተናጋጇን ኳታር በአል ባይት ስታዲየም ትገጥማለች።
የምድብ ሁለት የመጨረሻ ፍልሚያዎች ምሽት 4 ስአት ላይ ሲደረጉ ምድቡን በአራት ነጥብ የምትመራው እንግሊዝ 4ኛ ላይ ከተቀመጠችው ዌልስ ትጫወታለች።
በዚሁ ምድብ የሚገኙት የአሜሪካና ኢራን ፍልሚያ ግን ፓለቲካዊ አንድምታውም የጎላ ስለሆነ በበርካቶች ዘንድ ተጠባቂ ነው።
በ1980 ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የበጠሱት ሀገራት ጂኦፓለቲካዊ ተቃርኗቸው ሊፈታ አልቻለም።
በሰላማዊው መድረክ በፈረንጆቹ 1998 የአለም ዋንጫ ሲገናኙ ግን የተፈራው ሳይሆን የሀገራቱ ተጫዋቾች በአንድ ላይ ፎቶግራፍ ተነስተው ፓለቲካዊ ትኩሳቱን አብርደውት ነበር።
በኳታሩ የአለም ዋንጫ በአንድ ምድብ መደልደላቸው ከታወቀ ወዲህ ግን የከረመው እሰጣ አገባ መሰማት ጀምሯል።
ቴህራን የአሜሪካ የእግር ኳስ ፌደሬሽን በማህበራዊ ትስስር ገፁ ሰንደቄን በራሱ ፍላጎት ለመቀየር ሞክሯል በሚል አሜሪካ ከውድድሩ ውጭ እንድትሆን ለፊፋ አቤት እስከማለት ደርሳለች።
ጀርመናዊው የቀድሞው የአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የርገን ክሊስማን "ስፓርታዊ ጨዋነት የጎደለው ባህሪ በኢራን ስፓርት እንደ ባህል ተወስዷል" የሚል አስተያየቱን ለቢቢሲ መስጠቱም ኢራናውያንን አስቆጥቷል።
የካርሎስ ኬሮዥ ቡድን በአልቱማማ ስታዲየም የሚያደርገው ጨዋታ በነዚህ ስፓርታዊና ሌሎች ፓለቲካዊ አስተያየቶች የታጀበ ነው።
የሚመዘገበው ውጤትም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ከ24 አመት በፊት አሜሪካን 2 ለ 1 ያሸነፉት የፐርሺያ ኮከቦች ሜህዲ ታረሚ እና ሳርደር አዝሞንን ይዘው የ1998ቱን ድል ለመድገምና ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ይፋለማሉ።
በአለም የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ አሜሪካ 16ኛ ደረጃን ስትይዝ ኢራን 20ኛ ላይ ተቀምጣለች።