ቻይና፤ አሜሪካ ከፍተኛ “የኒውክሌር ስጋት” ነች አለች
ቻይና ፔንታጎን የቻይና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እና የባላስቲክ ሚሳይል ኃይል ጨምሯል በሚል ላወጣው ሪፖርት ምላሽ ሰጥታለች
ቻይና፤ አሜሪካ “የኒውክሌር ስጋት” በሚል ስሜን ለማጠልሸት እየሚከረች ነው ስትል ወቅሳለች
ቻይና በአሜሪካ የመከላከያ መ/ቤት ፔንታጎን፣ወታደዊ አቅሟ ማደጉን በሚመለከት ያወጣውን ሪፖርት ውድቅ አድርጋለች።
ቤጅንግ ሳይትሆን የኒውክሌር ውጥረትን የቀሰቀሰችው ዋሽንግተን ናት በማለት ሪፖርቱን አስተባብላለች።
የአሜሪካ መከላከያ ሚንስቴር በቅርብ ጊዜ ግምገማው የቻይናን ህዝባዊ ሪፐብሊክ የሚያካትት ወታደራዊ እና የደህንነት እድገቶችን በሚመለከት ሪፖርት አትሟል። ፔንታጎን እያደገ የመጣውን የቻይና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እና የባላስቲክ ሚሳይል ኃይል ጨምሮ በርካታ ምልከታዎችን አድርጓል።
ሪፖርቱ እንደገመተው ቻይና አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይል ኃይሏን ከ150 ወደ 300 በእጥፍ ያሳደገች ሲሆን በፈረንጆቹ 2035 አሁን ካላት ቁጥር ከ400 እስከ አንድ ሽህ 500 የኒውክሌር ጦሯን በአራት እጥፍ ለማሳደግ ትፈልጋለች።
ነገር ግን በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ሊዩ ፔንግዩ ሪፖርቱ "ከዚህ በፊት እንደነበሩት ተመሳሳይ ሪፖርቶች እውነታዎችን ችላ ያለና በአድሎአዊነት የተሞላ ነው" ሲሉ አጣጥለውታል።
ቃል አቀባዩ አሜሪካ ይህን ሪፖርት የ 'ቻይና የኒውክሌር ስጋት' ጽንሰ-ሀሳብን ለማበረታታት እየተጠቀመች ነው ሲሉም መውቀሳቸውን ኒውስዊክ ዘግቧል። አሜሪካ ሪፖርቱን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ፍንትው ብሎ የሚታየውን የህዝብ እይታ ለማደናገር እየተጠቀመች ነው ብለዋል።
"እንደ እውነቱ ከሆነ በዓለም ላይ ያለው የኒውክሌር ስጋት ዋነኛ ምንጭ ከራሷ ውጭ ሌላ የለም" ብለዋል ቃል አቀባይ ሊዩ።
አክለውም "አሜሪካ የዓለማችን ትልቁ እና እጅግ የላቀ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ቢኖራትም አሁንም መሳሪያዋን ለማሻሻል በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን በማፍሰስ ላይ ትገኛለች” ሲሉ ጣታቸውን ቀስረዋል።
እንደ ስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም መረጃ አሜሪካ በአጠቃላይ ወደ አምስት ሽህ 500 የሚጠጋ የኒውክሌር መሳሪያ ባለቤት ናት።ከእነዚህም ውስጥ በግምት አንድ ሽህ 744 የሚሆኑት በአሁኑ ጊዜ ተሰማርተው ይገኛሉ ተብሏል።