ፕሬዝደንት ባይደን የአሜሪካ ጦር ለጋዛ በአየር እርዳታ ሊያደርስ መሆኑን ገለጹ
እስራኤል እያካሄደች ባለው ጦርነት እስካሁን 30ሺ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል
የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድ በትናንትናው እለት በእስራኤል የአየር ድብደባ ሰባት የእስራኤል ታጋቾች ተገድለዋል ብሏል
ፕሬዝደንት ባይደን የአሜሪካ ጦር ለጋዛ በአየር እርዳታ ሊያደርስ መሆኑን ገለጹ።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የአሜሪካ ጦር በጋዛ እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች ምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለመጀመሪያ ጊዜ በአየር ለማቅረብ ማቀዱን አስታውቀዋል።
ፕሬዝደንት ባይደን ይህን እቅድ ይፋ ያደረጉት በጋዛ ውስጥ እርዳታ ለማግኘት ተሰልፈው የነበሩ ሰዎች ከተገደሉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
እስራኤል አድርሳዋለች በተባለው በዚህ በጥቃቱ ከ100 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድዋል።
ባይደን የአሜሪካ የአየር እርዳታ በቀጣይ ቀናት የሚካሄድ መሆኑን ከመግለጽ ውጭ ስለዝርዝር ጉዳዩ አልተናገሩም።ጆርዳንን እና ፈረንሳይን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ቀደም ብለው በአየር እርዳታ ማድረስ ጀምረዋል።
"ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፤ አሜሪካ ተጨማሪ ስራዎችን ትሰራለች" ያሉት ባይደን ወደ ጋዛ እየገባ ያለው እርዳታ በቂ አይደለም ሲሉ አክለዋል።
የኃይትሀውስ ቃል አቀባይ ጆን ክርቢይ እርዳታ በአየር የማድረስ ስራ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት፣ ከእስራኤል ጎን የተሰለፈችው አሜሪካ ተኩስ እንዲቆም ባትፈልግም፣ የሰብአዊ እርዳታ ግን እንዲገባ እንደምትፈልግ ገልጻለች።
የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድ በትናንትናው እለት በእስራኤል የአየር ድብደባ ሰባት የእስራኤል ታጋቾች ተገድለዋል ብሏል።
የእስራኤል ባለስልጣናት ሀማስ ለሚያወጣቸው ተመሳሳይ መግለጫዎች የሳይኮሎጂ ጦርነት ነው በሚል ምላሽ አይሰጡም።
እስራኤል በጋዛ ዘመቻ የከፈተችው ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ ቢያንስ 250 ሰዎችን አግቶ መውሰዱን እና 1200 ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ ነው።
እስራኤል እያካሄደች ባለው ጦርነት እስካሁን 30ሺ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ባለፈው ህዳር በተደረገው ለአንድ ሳምንት የቆየ ተኩስ ጋብ የማድረግ ስምምነት 100 እስራኤላውያን እና የውጭ ዜጎች መለቀቃቸው ይታወሳል። ታጋቾቹ እንዲለቀቁ እስራኤልም 240 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለቃለች።
አምስት ወራት ያስቆጠረውን የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት በስምምነት እንዲጠናቀቅ ጥረት ቢደረግም እስካሁን አልተሳካም።