የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ ሰባት ታጋቾች መገደላቸውን አስታወቀ
የእስራኤል ባለስልጣናት ሀማስ ለሚያወጣቸው ተመሳሳይ መግለጫዎች የሳይኮሎጂ ጦርነት ነው በሚል ምላሽ አይሰጡም
አቡ ኡባይዳ በቴሌግራም ገጹ በፖሰተው መግለጫ በእስራኤል የአየር ጥቃት እስካሁን የተገደሉ ታጋቾች ቁጥር 70 ደርሷል ብሏል
ሀማስ ወታደራዊ ክንፍ ሰባት ታጋቾች መገደላቸውን አስታወቀ።
እስራኤል እያደረገች ባለው የአየር ድብደባ በጋዛ ተይዘው የነበሩ ሰባት ታጋቾች መገደላቸውን የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሰም ብሬጌድ ቃል አቀባይ አቡ ኡባይዳ በትናንትናው እለት ተናገሩ።
ቃል አቀባዩ ታጋቾቹ መቼ እና የት እንደተገደሉ ግን ግልጽ አላደረገም።
አቡ ኡባይዳ በቴሌግራም ገጹ በፖሰተው መግለጫ በእስራኤል የአየር ጥቃት እስካሁን የተገደሉ ታጋቾች ቁጥር 70 ደርሷል ብሏል።
የእስራኤል ባለስልጣናት ሀማስ ለሚያወጣቸው ተመሳሳይ መግለጫዎች የሳይኮሎጂ ጦርነት ነው በሚል ምላሽ አይሰጡም።
እስራኤል በጋዛ መጠነሰፊ ዘመቻ የከፈተችው ባለፈው ጥቅምት ወር የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ ቢያንስ 250 ሰዎችን አግቶ መውሰዱን እና 1200 ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ ነው።
እስራኤል እያካሄደች ባለው ጦርነት እስካሁን 30ሺ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ባለፈው ህዳር በተደረገው ለአንድ ሳምንት የቆየ ተኩስ ጋብ የማድረግ ስምምነት 100 እስራኤላውያን እና የውጭ ዜጎች መለቀቃቸው ይታወሳል። ታጋቾቹ እንዲለቀቁ እስራኤልም 240 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለቃለች።
አምስት ወራት ያስቆጠረውን የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት በስምምነት እንዲጠናቀቅ ጥረት ቢደረግም እስካሁን አልተሳካም።