ሰሜን ኮሪያ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮቪድ 19 ተጠቂ መገኘቱን ይፋ አደረገች
በሰሜን ኮሪያ የተገኘው የኮሮና ቫይረስ የአዲሱ ኦሚክሮን ዝርያ ነው
በሀገሪቱ በጣም ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል
ሰሜን ኮሪያ በሀገሪቱ የመጀመሪያውን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መገኘቱን በዛሬው እለት ይፋ አድርጋለች።
በሰሜን ኮሪያ የተገኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያም አዲሱ “ኦሚክሮን” መሆኑን የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ይህንን ተከትሎም በሀገሪቱ በጣም ከባድ የተባለ ብሄራዊ ድንገተኛ አደጋ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን፤ ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉንም ሮይተርስ ዘግቧል።
የሰሜን ኮሪያ ኬ.ሲ.ኤን.ኤ የዜና ኤጀንሲ ይዞት በወጣው መግለጫ፤ በሀገሪቱ ላይ በጣም አሳሳቢ እና ድንገተኛ አደጋ ተከስቷል፤ ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ ለ2 ዓመት ከ3 ወራት ጥብቅ ጥበቃ የተደረገበት የድንገተኛ ወረርሽኝ መከላከያ መጣሱን ተጥሷል ብሏል።
በሀገሪቱ የኮቪድ 19 መገኘቱን የሚያሳየው ሪፖርት በሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሚመራው የሰራተኞች ፓርቲ በትናትናው እለት በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ መሆኑ ተነግሯል።
ይህንን ተከትሎም የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በመላው ሀገሪቱ ጥብቅ የሆን የእነቅስቀሴ ገደብ እንዲታወጅ ማዘዛቸው ተሰምቷል።
የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ ከተከሰተ ከሁለት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፤ ሰሜን ኮሪያ በሀገሪቱ በኮቪድ 19 የተያዘ ሰው እንዳለ ሪፖርት አድርጋ አታውቅም ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርትም 24 ነጥብ 7 ሚሊየን ህዝብ ባላት ሰሜን ኮሪያ እስካሁን ከ64 ሺህ 207 ሰዎች ላይ ናሙና ተወስዶ ሁሉም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን አመላክቷል።