ሰሜን ኮሪያ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮና ሞት መመዝገቡን አስታወቀች
ከፍተኛ የሰውነት ትኩሳት የነበረባቸው 6 ሰዎች መሞታቸውን ሰሜን ኮሪያ ገልጻለች
ትኩሳታቸው ከፍተኛ የሆነ 187 ሺህ ሰዎች ለብቻ ተለይተው ክትትል እየተደረገባቸው ነው
በሰሜን ኮሪያ በኮቪድ-19 የመጀመሪያውን ሞት መመዝገቡን እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የትኩሳት ምልክቶች እየታየባቸው መሆኑን የሀገሪቱ የመንግስት ሚዲያ ዘግቧል።
እስካሁንም ከፍተኛ የሰውነት ትኩሳት ይታይባቸው የነበሩ 6 ሰዎች መሞታቸውን ያስታወቀችው ሰሜን ኮሪያ፤ ከእነዚህም ውስጥ አንድ ግለሰብ ላይ የኦሚክሮን ዝርያ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶበት እንደነበረ ተገልጿል።
ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት የታየባቸው 187 ሺህ ሰዎች ደግሞ ለብቻቸው ተለይተው የህክምና ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑንም በዘገባው ተመላክቷል።
የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት የኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ ውስጥ መከሰቱን በትናትናው እለት ቢያሰውቁም፤ የዘርፉ ባለሙያዎች ግን ቫይረሱ በሀገሪቱ ከተከሰተ ዋል አደር ሳይል አይቀርም ይላሉ።
የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት በትናትናው እለት ይፋ ባደረጉት መረጃ በዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ ውስጥ የኦሚክሮን ዝርያ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ገልጸዋል።
የሰሜን ኮሪያ የዜና ኤጀንሲ ዛሬ ባወጣው መረጃ ከዋና ከተማዋ ውጪ የቫይረሱ ምልክቶች የታየባቸው ሰዎች መገኘታውን አስታውቋል
በሀገሪቱ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን የሚያሳየው ሪፖርት በሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሚመራው የሰራተኞች ፓርቲ በትናትናው እለት በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ይፋ የተደረገው።
ይህንን ተከትሎም የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በመላው ሀገሪቱ ጥብቅ የሆን የእንቅስቀሴ ክልከላ እንዲታወጅ ማዘዛቸው ተሰምቷል።
የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ ከተከሰተ ከሁለት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፤ ሰሜን ኮሪያ በሀገሪቱ በኮቪድ 19 የተያዘ ሰው እንዳለ ሪፖርት አድርጋ አታውቅም ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርትም 24 ነጥብ 7 ሚሊየን ህዝብ ባላት ሰሜን ኮሪያ እስካሁን ከ64 ሺህ 207 ሰዎች ላይ ናሙና ተወስዶ ሁሉም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን አመላክቷል።