ባላስቲክ ሚሳዔሉ በሰዓት 13 ሺህ 119 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ መሆኑ ተንግሯል
ሰሜን ኮሪያ ወደ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻዋ ባሊስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏን የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታወቀ።
የሴኡል ወታደራዊ አመራሮች እንዳሳወቁት ሰሜን ኮሪያ የባላስቲክ ሚሳዔሉን በፒዮንግያንግ ሱናን አካባቢ ከጠዋቱ 12፡03 አካባቢ ነው ያስወነጨፈችው።
የጃፓን የባህር ዳርቻ ጠባቂዎችም ሰሜን ኮሪያ ከባድ መሳሪያ መተኮሷን አረጋግጠው፤ የተተኮሰው መሳሪያ ባሊስቲክ ሚሳኤል ሊሆን ይችላል ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ አመራሮች፤ ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈችው አዲሱ የባላስቲክ ሚሳዔል በ780 ኪሎ ሜትር ከፍታ 470 ኪሎ ሜትር መብረሩን ያስታወቁ ሲሆን፤ ሚሳዔሉ በሰዓት 13 ሺህ 119 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሰሜን ኮሪያ የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ከገባ ባለፉት 5 ወራት ውስጥ የዛሬውን ጨምሮ 14 የሚሳዔል ሙከራዎችን ማድረጓ ይታወሳል።
ፒዮንግ ያንግ ባሳለፍነው ወር ከፈረንጆቹ 2017 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳዔል ማስወንጨፏም ይታወሳል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከቀናት በፊት በተከበረው የሀገሪቱ ጦር ሃይሎች ምስረታ ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፤ “ፒዮንግያንግ አሁንም ቢሆን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እድገትን ለማፋጠን ጠንክራ ትሰራለች” ማለታቸው ይታወሳል።
ሰሜን ኮሪያ ባለፍነው ወር “አውሬው” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ግዙፉን ህዋሰኦንግ-17 አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል (አይ.ሲ.ቢ.ኤም) ሙከራ ማድረጓ ይታወሳል።
የዘርፉ ባለሙያዎች “ህዋሰኦንግ-17” ሚሳዔልን “ግዙፉ” ወይም “አውሬው” ሲሉ የሚጠሩት ሲሆን፤ ሚሳዔሉ አህጉር አቋራጭ (አይ.ሲ.ቢ.ኤም) ሚሳዔል አይነት ነው።