አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያለውን ውጥረት ተከትሎ ወደ ቀጠናው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ አሰማራች
ደቡብ ኮሪያ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠችም ተብሏል
አሜሪካ በኮሪያ ባሕረ ሰላጤ የምታርገውን ወታደራዊ ስምሪትና ልምምድ ሰሜን ኮሪያ ስትቃወም ቆይታለች
ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ ሚሳኤል ማስወንጨፏን ተከትሎ ስጋት የገባት አሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ ቀጠናው ማሰማራቷ ተሰማ።
በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሊንከን ስም የተሰየመው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ ኮሪያ ባሕረ ሰላጤው እንዲሰማራ ትዕዛዝ ተሰጥቷል ተብሏል።
ዋሸንግተንና ፒንግያንግ ውጥረት ውስጥ በመግባታቸው በቀጠናው ያለውን ውጥረት ግምት ውስጥ ያስገባ ስምሪት ተደርጓል ተብሏል።
አብርሃም ሊንከን የሚባለው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ከጃፓን ባሕር ኃይል ጋር በትብብር ወታደራዊ ስራ እየሰራ እንደሆነ ተገልጿል።
ዋሸንግተን እና ቶኪዮ ይህንን ወታደራዊ ስራ እያከናወኑ ያሉት የኢንዶ ፓሲፊክ አካባቢን ነጻና ክፍት ለማድረግ ነው ተብሏል። በጃፓን ባሕር ላይ እየተደረገ ያለው ልምምድና ትብብር የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነታቸውን ለማጠናከር መሆኑ ተገልጿል።
ጃፓን እና አሜሪካ በአካባቢው የሚያደርጉት ወታደራዊ ትብብር ወደፊት ሊመጣ የሚችል ጥቃትን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል ለማድረግ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ ኮሪያ ባሕረ ሰላጤ የተሰማራው ከ2017 ወዲህ የአሁኑ የመጀመሪያ ነው። በአውሮፓውያኑ 2017 አውሮፕላን የሚሸከመው የአሜሪካ መርከብ ፤ በደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን አካባቢ ባለው ባሕር ላይ ተሰማርቶ እንደነበር ተገልጿል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት፤ ሰሜን ኮሪያ በሚቀጥሉት ቀናት የመሬት ውስጥ የኒዩክለር ሙከራ ልታደርግ ትችላለች የሚል ከፍተኛ ፍራቻ እዳላቸው ተገልጿል።
የምዕራባውያን ስጋት የሆችው ሰሜን ኮሪያ ከ 2017 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አህጉር አቋራጭ ባልስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏ በቀጠናው ያለውን ውጥረት በድጋሚ ቀስቅሶታል እየተባለ ነው።
የደቡብ ኮሪያ መከላከያ መስሪያ ቤት፤ አሜሪካ ወደ ቀጠናው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ታሰማራለች መባሉን ተከትሎ አስተያየት አልሰጠም ተብሏል።
ከዚህ ቀደም አሜሪካ በኮሪያ ባሕረ ሰላጤ የምታርገውን ወታደራዊ ስምሪትና ልምምድ ሰሜን ኮሪያ ስትቃወም እንደነበር ይታወሳል።