“አሜሪካ በነፃነት ቀኗ ከኮሮና ቫይረስ ነፃ ትሆናለች”-ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን
ፕሬዚዳንቱ ኮሮና ወረርሽኝ ሆኖ የታወጀበትን 1ኛ አመት ምክንያት በማድረግ ንግግር አሰምተዋል
ግማሽ ሚልዮን የሚሆኑ አሜሪካውያን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካ የነፃነት ቀን በምታከብርበት ቀን ከኮሮና ቫይረስ ነፃ እንደምትሆን ያላቸው ተስፋ ገለፁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ኮሮና ቫይረስ አለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ የታወጀበትን አንደኛ አመት ምክንያት በማድረግ ንግግር አሰምተዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ክትባት ከወሰዱ፤ አሜሪካ የነፃነት ቀን በምታከብርበት ሀምሌ 4 ከቫይረሱ ነፃ መሆኗ ታውጃለች ብለዋል፡፡
ለዚህም እስከ መጪው ግንቦት 1 ቀን በሁሉም የሀገሪቱ ግዛቶች ያሉ ጎልማሳዎች ክትባት እንዲያገኙ መመሪያ እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ሲሰጥ የነበረው ክትባት በእድሜ ለገፉ አረጋውያንና የጤና እክል ላለባቸው ሰዎች ትኩረት ያደረገ እንደነበር በማስታወስ፡፡ ፕሬዝዳንቱ ያደረጉት ንግግር ታድያ አሁንም በአሜሪካ መጠነኛ የሰዎች መሰባሰብ ተመልሶ እውን የሚሆኑበት ቀን በጉጉት እንዲጠበቅ ያደረገ ቀጠሮ ተደርጎ በበርካቶች ዘንዳ ተጠብቋል፡፡
ባይደን “ይህ በተባበረ መንፈስ ከተወጣነው ሀምሌ 4 ፡ እናንተ፤ቤተሰቦቻችሁና ጓደኞቻችሁ፡ አንድ ላይ በየጎዳናው ሆናችሁ የነጻነት ቀናችሁን ታከብራለችሁ”ም ብለዋል።የአሜሪካ የነፃነት ቀን ብቻ ሳይሆን “ከቫይረሱ ነፃ የወጣችበት” ቀን ይሆናልም ብለዋል ፕሬዝዳንት ባይደን፡፡ ግማሽ ሚልዮን የሚሆኑ አሜሪካውያን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡