ትራምፕ በከፍተኛ ልዩነት ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ ባይደን ለመጀመርያ ጊዜ ህዝባዊ ንግግር ሊያደርጉ ነው
በምርጫው ሽንፈት የገጠማቸው ሃሪስ የትራምፕን ራዕይ ባልደግፍም የስልጣን ሽግግር ሂደቱን አግዛለሁ ብለዋል
በመጪዎቹ ቀናት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ካቤኔያቸውን ለማዋቀር ሹመት የሚሰጡ ይሆናል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፓርቲያቸው ዴሞክራት በሪፐብሊካኑ እጩ ዶናልድ ትራምፕ ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ህዝባዊ ንግግር ሊያደርጉ ነው፡፡
የትራምፕ ድል መረጋገጡን ተከትሎ ባይደን እና ምክትላቸው ሃሪስ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን ልከዋል፡፡
በዘንድሮውም ምርጫ ቀዳሚ የዴሞክራት ዕጩ ሆነው የቀረቡት ጆ ባይደን ከትራምፕ ጋር ካደረጉት የምርጫ ክርክር በኋላ በአጠቃላይ የአዕምሮ እና አካላዊ ሁኔታቸው ላይ ሀሳብ የገባው ፓርቲው በካማላ ሃሪስ እንዲተኩ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ባይደን በንግግራቸው አጠቃላይ ስለምርጫ ሁኔታው ፣ እየተጠናቀቀ ስለሚገኘው የስልጣናቸው ሁኔታ እንዲሁም ሌሎች ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ህዝባዊ ንግግር እንደሚያደርጉ ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
በተጨማሪም ቀኑ መች እንደሆነ ይፋ ባይሆንም ከተመራጩ ፕሬዝዳንት ጋር ለመምከር ባይደን ግብዣ ማቅረባቸውን የትራምፕ የምርጫ አስተባባሪዎች አስታውቀዋል፡፡
በነጩ ቤት መንግስት የሚቀመጡ የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብለው ሲጠበቁ ሽንፈት የገጠማቸው ሃሪስ ከምርጫው በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸውም በአለ ሲመቱ እስከሚካሄድበት ጥር 20 ድረስ በሚኖረው ሽግግር እና የስልጣን ርክክብ ትራምፕን ለማገዝ ቃል ገብተው፤ ነገር ግን ትራምፕ ለሀገሪቷ ያለውን ራዕይ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከማክሰኞው ምርጫ በፊት የተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች በምርጫው ሁሉቱም ዕጩዎች እኩል የማሸነፍ እድል እናዳላቸውና ከፍተኛ ትንቅንቅ የሚደረግበት ምርጫ እንደሚካሄድ አመላክተው ነበር።
ሆኖም የትራምፕ በከፍተኛ ልዩነት ወደ ነጩ ቤተ መንግስት መመለስ አሜሪካውያን በኢኮኖሚያቸው ምን ያህል ቅር እንደተሰኙ ፣ የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ደረጃ መድረሱንና በድንበር ደህንነት እና በውጩ ጉዳይ ፖሊስ የትራምፕን ሀሳብ መግዛታቸውን የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡
ትራምፕ የፕሬዝዳንትነቱን ስፍራ ለማግኙት ወሳኝ ከሆኑ 7 ግዛቶች አምስቱን በማሸነፍ አሁንም ድምጽ እየተሰበሰበ በሚገኝበቸው አሪዞና እና ኔቫዳ እየመሩ ይገኛሉ፡፡
በቀጣዮቹ ቀናት እና ሳምንታት ትራምፕ ካቢኔያቸውን ለማወቀር በእርሳቸው መሪነት ስር የሚያገለግሉ ሰዎችን እንደሚመርጡ ይጠበቃል።
የቴስላ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቢሊየነሩ ኢለን መስክ በአስተዳደራቸው ውስጥ ሀላፊነት ከሚሰጣቸው መካከል አንዱ ሲሆን እንዲሁም የቀድሞው የፕሬዝዳንት እጩ ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየርም ስልጣን ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ባለፈም የቀድሞ አስተዳደራቸው ባልደረባ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ማይክ ፖምፒዮ እና ሮበርት ኦብራይን ወደ ሀላፊነት እንደሚመለሱ ከሚጠበቁ ሰዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡