ትራምፕ በ2018 ሀገራቸውን ከኢራን የኒዩክሌር ስምምነት ማስወጣታቸው ይታወሳል
ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ 47ኛው ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ከተገለጸ በኋላ የሀገራት መሪዎች የደስታ መልዕክታቸውን እየገለጹ ነው።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም ታሪካዊ ድል አስመዝግበዋል ላሏቸው ትራምፕ የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክታቸውን በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። የእስራኤልና አሜሪካ ትብብርም በትራምፕ የስልጣን ዘመን ይበልጥ እንደሚያድግ ተስፋ መሰነቃቸውን የሚያሳይ መልዕክት ልከዋል።
የእስራኤል ባላንጣ ኢራን ለትራምፕ የደስታ መግለጫ ባትሰድም የትራምፕ መመረጥ የቀደሙ ስህተቶችን ለማረም እድል ይሰጣል ብላለች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባግሄይ “ኢራን በተለያዩ አሜሪካ መንግስታት ፖሊሲዎችና አመለካከቶች ምክንያት እጅግ ተጎድታለች፤ የትራምፕ መመረጥ እነዚህን ስህተቶች ለማረም እድል ሊፈጥር ይችላል” ማለታቸውን ኢርና የተባለው የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የኢራን መንግስት ቃልአቀባዩዋ ፋቴሜህ ሞሃጀራኒ በበኩላቸው “የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለኢራናውያን ግድ የሚሰጠን ጉዳይ አይደለም፤ አስቀድመን ወሳኝ ግምት አድርገናል፤ (ምርጫው) በህዝባችን ላይ የሚያሳድረው አንዳች ተጽዕኖ የለም” ብለዋል።
የቴህራን ባለስልጣናት ይህን ይበሉ እንጂ ትራምፕ ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት ሲገቡ በኢራን የነዳጅ ኢንዱስትሪዎች ላይ ጠንከር ያሉ ማዕቀቦችን በመጣል እስራኤል የቴህራንን የኒዩክሌር ጣቢያዎች እንድትመታ ሊያበረታቱ እንደሚችሉ ተንታኞች ያነሳሉ።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ ቴህራን እና የቀጠናው አጋሮቿ (የታጠቁ ሃይሎች) ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውን አመላክቷል።
“ጺዮናውያኑ (እስራኤል) እኛን ለመዋጋት አቅም የላቸውም፤ የመሳሪያ ክምችታችን ከበቂ በላይ ነው፤ ምላሻችን ይጠብቁ” ሲሉ የአብዮታዊ ዘቡ ምክትል ሃላፊ አሊ ፋዳቪ መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ምክትል ሃላፊው ኢራን አራት ወታደሮቿ ለተገደሉበት የጥቅምት 25ቱ የእስራኤል ጥቃት የአጻፋ እርምጃ ለመውሰድ የያዘችውን እቅድ እንዳልሰረዘችውም ነው የገለጹት።
ከ1979ኙ የኢራን አብዮት ጀምሮ የሻከረው የአሜሪካ እና ኢራን ግንኙነት ዶናልድ ትራምፕ የ2016ቱን ምርጫ አሸንፈው ወደ ዋይትሃውስ ከገቡ በኋላ ይበልጥ ተባብሷል።
ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው ለእስራኤል የሚበጁ ኢራንን ደግሞ የሚጎዱ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል። በ2018ም አሜሪካን ከ2015ቱ የኢራን የኒዩክሌር ስምምነት በማስወጣት ቴህራን ተነስተውላት የነበሩ ማዕቀቦች ዳግም ተፈጻሚ እንዲሆኑ አድርገዋል።
በ2020 ትራምፕ የኢራን አብዮታዊ ዘብ መሪው ቃሲም ሱሌማኒ በኢራቅ ባግዳድ እንዲገደሉ ትዕዛዝ መስጠታቸውም ቴህራን በሪፐብሊካኑ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ላይ ጥርሷን እንድትነክስባቸው ማድረጉ የሚታወስ ነው።