የትራምፕን ድል ተከትሎ የኤለን መስክ ሀብት በ20 ቢሊየን ዶላር ጨመረ
የቴስላ እና ኤክስ ባለቤቱ ከ120 ሚሊየን ዶላር በላይ ለትራምፕ የቅስቀሳ ቡድን በማዋጣት በብዙው አትርፏል ተብሏል
ትራምፕ ማሸነፍ በተለይ ከክሪፕቶከረንሲ ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለጠጎች ሀብት እንዲመነደግ አድርጓል
ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆናቸው መነገሩን ተከትሎ የአለማችን ቢሊየነሮች ሀብት ተመንድጓል።
ፎርብስ ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ትራምፕን የደገፈው ኤለን መስክ በአንድ ቀን ብቻ 21 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ሀብት ማግኘቱን አመላክቷል።
ሽንጡን ገትሮ የተከራከለትና በየመድረኩ የተናገረለት ትራምፕ ማሸነፍ የቢሊየነሩን አጠቃላይ ሀብት 285.6 ቢሊየን ዶላር አድርሶት የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር እንዲሆን አድርጎታል።
ለዚህም የቴስላ የአክሲዮን ዋጋ በ15 በመቶ መጨመር ዋነኛው ምክንያት ነው ብሏል ፎርብስ በዘገባው።
ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን 120 ሚሊየን ዶላር መለገሱ የሚነገርለት ኤለን መስክ፥ ጥቂት ሰጥቶ ብዙ በብዙው ማትረፍ ችሏል።
ትራምፕ ዳግም ወደ ዋይትሃውስ ከገቡ ለመስክ የመንግስት ስልጣን እንደሚሰጡ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
በሪፐብሊካኑ እጩ ማሸነፍ ኤለን መስክ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአለማችን ቀዳሚ ባለጠጎችም በአንድ ቀን ሀብታቸው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
በተለይ ከክሪፕቶከርንሲ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቢሊየነሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጸው ፎርብስ፥ ትራምፕ በቅስቀሳቸው የክሪፕቶከረንሲ ታክስ እቀንሳለሁ ማለታቸውን አስታውሷል።
ከኤለን መስክ ባሻገር የነማን ሀብት ተመነደገ?
- ጄፍ ቤዞስ - ቤዞስ የትራምፕ ድል 7 ቢሊየን ዶላር አስገኝቶለታል። የአማዞን አክሲዮኖች ሽያጭ በ3.8 በመቶ ማደጉም የቤዞስን ሀብት 223.5 ቢሊየን ዶላር አድርሶት ከመስክ በመቀጠል የአለማችን ሁለተኛው ቢሊየነር ሆኗል።
- ሌሪ ኢሊሰን - የኦራክል መስራች ደግሞ በአንድ ቀን 12 ቢሊየን ዶላር አግኝቷል። አጠቃላይ ሀብቱ 220.8 ቢሊየን ዶላር የደረሰው ላሪ ከቤዞስ ጋር የነበረውን የሀብት ልዩነት አጥብቦ በፎርብስ የቢሊየነሮች ደረጃ ሶስተኛ ላይ ተቀምጧል።
- ዋረን ቡፌት - አሜሪካዊው ታዋቂ ኢንቨስተር ቡፌት በበኩሉ የትራምፕ ድል 7.6 ቢሊየን ዶላር አስገኝቶለታል። አጠቃላይ ሀብቱም 147.4 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።
- ብሪያን አርምስትሮንግ - ኮይንቤዝ የተሰኘው የክሪፕቶ መገበያያ ስራ አስፈጻሚው ብሪያን አርምስትሮንግ በትናንትናው እለት 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር አግኝቶ አጠቃላይ ሀብቱ 11 ቢሊየን ዶላር ደርሷል። የኮይንቤዝ ሌላኛው መስራች ፍሬድ ኢርሳምም 600 ሚሊየን ዶላር አግኝቷል።
- ሚኬል ሴይለር - የቢትኮይን ስትራቴጂ ኩባንያው ማይክሮ ስትራቴጂ መስራቹ ሴይለር በትራፕም ማሸነፍ 600 ሚሊየን ዶላር ወደ ካዝናው አስገብቶ አጠቃላይ ሀብቱም 6.6 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።