ክስ የቀረበባቸው ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ወንጀሉን ፈጽሞ እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል
ዶናልድ ትራምፕ ሌላ የአስገድዶ መድፈር ክስ ቀረበባቸው፡፡
የአሜሪካ 45ኛው ፕሬዝዳንት በመሆን ከፈረንጆቹ 2016 እስከ 2020 ድረስ የገለገሉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር የምርጫ ቅስቀሳቸውን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በዶናልድ ትራምፕ ላይ ከዚህ በፊት የወሲብ ፊልም ተዋናይ ለሆነችው ስቶርም ዳንኤልስ ከተባለች እንስት ጋር የፈጸሙት ድርጊት ለህዝብ ይፋ እንዳይሆን በድብቅ ክፍያ ፈጽመው ግብር አጭበርብረዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
አሁን ደግሞ በፋሽን ጉዳዮች ዙሪያ ጸሃፊ የሆኑት ጂን ካሮል የተሰኘች እንስት ከ28 ዓመት በፊት በዶናልድ ትራምፕ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል፡፡
የተፈጸመባቸውን የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ጉዳይ እስካሁን ዝም በማለታቸው እንደሚጸጸቱም ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የ79 ዓመቷ ጂን ካሮል በአስገድዶ መደፈር ወንጀሉ በተፈጸመባቸው ወቅት የነበረው ስሜት አሁን ድረስ እንደሚሰማቸው የተናገሩ ሲሆን በመልበሻ ክፍል ውስጥ የውስጥ ልብስ እየለኩ እያለ በትራምፕ መደፈራቸውን ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ ዶናልድ ትራምፕ ሊደፍርዎት ሲሞክር ሊያስቆሙት አልሞከሩም? በሚል ከጠበቃ ለቀረበላቸው ጥያቄ ካሮል “አቁም ያልኩት ይመስለኛል፣ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ምን እንዳልኩት አሁን አላስታውስም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የትስስር ገጻቸው ድርጊቱ ሆን ተብሎ የተፈጠረ ክስ መሆኑን እና ጂን ካሮል እኔ የምፈልጋት አይነት ሴት አይደለችም ሲሉ ጽፈዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት አክለውም እኔ አንቺን ስደፍር ያየ ሰው የለም? በግንኙነታችን ወቅትስ እርካታ ነበረሽ? ሲሉም ተሳልቀዋል ተብሏል፡፡
የዶናልድ ትራምፕን ምላሽን ተከትሎም ጠበቃቸው እንዲህ አይነት ምላሽ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ያሳሰበ ሲሆን የማንሀተን አቃቢ ህግ ቢሮም ዶናልድ ትራምፕ የሰዎችን ክብር እንዲጠብቁ አስጠንቅቋል፡፡