ትራምፕ ለቀድሞዋ የጋዜጣ አምደኛ ጂን ካሮል 5 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ተወሰነ
የማንሃተን ፍርድ ቤት ዶናልድ ትራምፕ በካሮል ላይ ፈፅመውታል ላለው ወሲባዊ ትንኮሳና ስም ማጥፋት ነው ቅጣቱን ያሳለፈው
የቀድሞው ፕሬዝዳንት እና ጠበቆቻቸው ግን ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ ገልፀዋል
አወዛጋቢው የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የ2024ቱ ምርጫ ተሳትፏቸውን የሚያደበዝዝ ጉዳዮች እየገጠሟቸው ነው።
በስቶርሚ ዴኔልስ በቀረበባቸው የወሲብ ቅሌት ክስ ፍርድቤት የቀረቡት ትራምፕ፥ በትናንትናው እለት ደግሞ በጂን ካሮል መሰል ክስ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
ካሮል ከ30 አመት በፊት ትራምፕ በማንሃተን በሚገኝ ውድ ልብሶች መሸጫ መደብር ውስጥ አስገድዶ ደፍሮኛል የሚል ክስ ማቅረቧ ይታወሳል።
ከዚህም ባሻገር ባለፈው አመት ይህንኑ ጉዳይ በሚዲያ ሳቀርብ "ውሸታም ነች" ብሎ ስሜን አጥፍቷል የሚል ክስም ተያይዞ ቀርቧል።
በኒውዮርክ ማንሃተን የሚገኘው ፍርድቤትም ጉዳዩን ሲመረምር ቆይቶ ትናንት በሰጠው ውሳኔ፥ አስገድዶ ደፍሮኛል በሚል የቀረበው ክስ ትራምፕን ተጠያቂ የሚያደርግ ሆኖ አላገኘሁትም ብሏል።
ይሁን እንጂ በወሲባዊ ትንኮሳ እና ስም የማጠልሸቱ ክስ ጥፋተኛ ተብለው ትራምፕ ለካሮል 5 ሚሊየን ዶላር እንዲከፍሉ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
ካሮል ከውሳኔው በኋላ በሰጡት አስተያየት "አሁን አለም እውነቱን አውቋል፤ ውሳኔው ለእኔ ብቻ ሳይሆን ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው ሲናገሩ ሰዎች ለማያምኗቸውም ጭምር ዋጋ አለው" ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ክሱ ሲታይ ፍርድ ቤት ያልቀረቡት ትራምፕ "ይቺ ሴት ማን እንደሆነች በፍፁም የማውቀው ነገር የለም፤ የፍርድ ቤቱ ውሳኔም አሳፋሪ ነው" ሲሉ በራሳቸው የማህበራዊ ትስስር ገፅ ትሩዝ ሶሻል ላይ ፅፈዋል።
ጠበቃቸው ጆይ ታኮፒያም ትራምፕን ከአስገድዶ መድፈር ክሱ ነፃ ያላቸው ፍርድቤት ያሳለፈው ውሳኔ አስገራሚ ነው ብለዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የማንሃተን ፍርደቤት ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁም ነው ያነሱት።
የትናንቱ ውሳኔ በ2024 በድጋሚ አሜሪካን ለመምራት በምርጫ እፎካከራለሁ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ተቀባይነት ላይ ጥቁር አሻራ እንደሚያሳርፍ እየተነገረ ነው።