ፕሬዝዳንት ባይደን ፑቲን “በቀናት ውስጥ ዩክሬንን እንደሚወሩ እርግጠኛ ነኝ” አሉ
"እስካሁን ድረስ፡ እሱ (ፑቲን) ውሳኔውን እንዳሳለፈ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል ጆ-ባይደን
በሩሲያ የሚደገፉ ተገንጣዮች በተነጠሉ ግዛቶች ያሉት ሲቪሎች ወደ ሩሲያ እንዲወጡ ማድረጋቸው ምእራባውያንን ስጋት ውስጥ ከቷል
የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን በቀናት ውስጥ ዩክሬንን ለመውረር ወስኗል ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ፡፡
ባይደን ይህን ያሉት በሞስኮ የሚደገፉ ተገንጣዮች በተነጠሉ ግዛቶች ላይ የሚገኙት ሲቪሎች አከባቢያቸውን ለቀው በአውቶቡሶች እንዲወጡ ከተናገሩ በኋላ ነው፡፡
በዶኔትስክ እና በሉሃንስክ የሚገኙ ተገንጣይ መሪዎች ባወጡት የቪዲዮ መግለጫ እንዳሉት ከሆነ ግን በግዛቶቹ የነበሩ ሰዎች እንዲወጡ የተደረገው ዩክሬን በግዛቶቹ ላይ በቅርቡ ጥቃት ልትሰነዝር መዘጋጀቷ ስለተደረሰበት ነው ሲሉ ዩክሬንን ሲከሱ ተደምጧል፡፡
ኪቭ የተገንጣይ መሪዎች ክስ ውሸት ነው ስትል አስተባብላለች፡፡
ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በዘርፈ ብዙ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ እንደምትገኝ የሚነገርላት ሩሲያ፤ኪቭ ወደ ኔቶ ለመቀላቀል የምታደርገውን ጉዞ ማቆም ትፈልጋለች፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሩሲያ ‘በዩክሬን ጉዳይ’ ከምእራቡ ዓለም ጋር ከፍተኛ ውጥረት ላይ መግባቷን ተከትሎ በምእራባውያን በኩል የሚቀርብላትን የ“ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ነው” ክስ ስታብጠለጥል ቆይታለች፡፡
ምዕራባውያንን የመውረር እቅድ የለኝም ስትልም በውጭ ጉዳይ መስርያ ቤቷ በኩል ስትግለጽ ቆይታለች፡፡
ሩሲያ እንዲህ ብትልም ግን አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የምእራቡ ዓለም ሀገራት በሩሲያ ላይ ያላቸውን ስጋት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
አርብ ዕለት በዶኔትስክ እና ሉሃንስክ ከተሞች የአማፂያኑ መሪዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ሩሲያ የማስወጣታቸው ድርጊትም፤ ጉዳዩ ይበልጥ እንዲባባስ እና በኃያላኑ ሀገራት መከከል ያለውን ውጥረት ምናልባትም ወደ ከፋ ጦርነት እንዳይወስደው ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡
ይህን የአማጽያን ድርጊት ተከትሎም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን የሩሲያ ጦር በሚቀጥሉት ቀናት ዩክሬንን ያጠቃል ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግሯል።
"እስካሁን ድረስ፡ እሱ (ፑቲን) ውሳኔውን እንዳሳለፈ እርግጠኛ ነኝ" ም ብለዋል፡፡
የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ ፡በትናትናው እለት የሩስያ ልዩ ሃይሎች በዶኔትስክ በሚገኙ የማህበራዊ መሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ፈንጂዎች ስለጠመዱ ነዋሪዎቹ እቤት እንዲቆዩ ማሳሰቡ አይዘነጋም፡፡
የሩሲያ የፌደራል ደህንነት አገልግሎት በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም፡፡
የሩሲያ የዜና ኤጀንሲዎች በዩክሬን የሚገኙ ሪፖርተሮቻቸውን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት ከሆነ ግን፤ ከዩክሬን ከተገነጠለችው የሉሃንስክ ሪፐብሊክ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ አንዷ በሆነችው ሉሃንስክ እና በአካባቢው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ክፍል ሁለት ፍንዳታዎች መድረሳቸውን አስታውቋል።
የዋይት ሀውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ጄን ፓሳኪ የተገንጣዮች ድርጊት የእኛ (አሜሪካ)ን ጥርጣሬ የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
ጄን ፓሳኪ "ሩሲያውያን ለጦርነት ሽፋን ሚሆኗቸው ሰበቦች ሊፈልጉ እንደሚችሉ ከተነበይን ረዥም ጊዜያት ሆኖናል” ሲሉም ለጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡