አሜሪካ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለመስጠት እያጤነች መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤቷ በኩል ገልጻለች
ሩሲያ የአሜሪካ ምክትል አምባሳደርነም ከሞስኮ ማባረሯን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር መስርያ ቤት አስታወቀ።
ሩሲያ ያባረቻቸው ከፍተኛ ዲፕሎማት በሞስኮ የአሜሪካ ኤምባሲ የሚሽኑ ምክትል ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ የነበሩትን ባርት ጎርማንን መሆኑም ተነግሯል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ቃል አቀባይ "ሩሲያ በእኛ ዲፕሎማት ላይ የወሰደችው እርምጃ ነገሮች የሚያባብስ ነው፤ እኛም ምላሻችንን እያጤንን ነው" ብለዋል።
አር.አይ. ኖቮስቲ የተሰኘ የሩሲያ የዜና ወኪል ከሞስኮ የተባረሩት ከፍተኛው ዲፕሎማት ላለፉት ሶስት ዓመታት በኤምባሲው ሁለተኛ ሰው ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው።
እርምጃው የተወሰደው በዋሽንግተን እና በሞስኮ መካከል በዩክሬን ጉዳይ ከፍተኛ ውጥረት በነገሰበት ወቅት ነው።
ምዕራባዊያን ሀገራት ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ትችላለች ሲሉ፤ አሜሪካ ደግሞ ሞስኮ ወረራውን በአየር ጥቃት ልትከፍት ትችላለች ስትል እያስጠነቀቀች ነው።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸው ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ አሳስበዋል፤ አንዳንዶች ደግሞ የኤምባሲ ሠራተኞቻቸውን ከዋና ከተማዋ ኪዬቭ አሽሽተዋል።
ምእራባውያን ዩክሬን ባለው ጉዳይ ዜጎቻቸው በማስወጣት ረግድ በርካታ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ቢሆኑም ግን ችግሩ ይፈጠርባታል የተባለቸው ዩክሬን “ምንም የተለወጠ ነገር የለም ስለዚህም ማንም ሰው ሀገሪቱን ለቆ መውጣት የለበትም” እያለች ነው።
ከዛም አልፎ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት በጠረጴዛ ዙርያ ለመወያት ዝግጁ መሆኗ እየገለጸች ነው።
የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ በጥቂት ቀናት ዩክሬንን ልትወር ነው የሚባለው “ማስረጃ የሌለው ወሬ ነው” ሲሉ አጣጥለዋል።
ሞስኮ በአንጻሩ ወረራ የሚባል ነገር በሀሳቤም የለም ስትል ተደምጣለች።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊከን የሩሲያ ጠብ አጫሪነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ቀደም ሲል መናገራቸው የሚታወስ ነው።
የሩሲያ ጥቃት በማንኛውም ቅጽበት ሊጀመር እንደሚችል በተለይም በፌብሩዋሪ 20 የኦሎምፒክ ፍጻሜ ዕለት ሊሆን እንደሚችል ምልክቶች አሉ ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡
አሜሪካ ለዚህ ጥቃት ምላሽ 3 ሺህ የሠራዊት አባላትን ከኖርዝ ካሮላይና ቀጠና ወደ ፖላንድ አንቀሳቅሳለች። ይሁንና እነዚህ ወታደሮች ከዩክሬን ወታደሮች ጋር ተሰልፈው ይዋጋሉ ወይስ አይዋጉም ለሚለው ግልጽ የሆነ ነገር የለም።