ሞስኮ ከ100 ሺህ የሚልቁ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ድንበር ማስጠጋቷ አውዳሚ ጦርነት እንዳይገባ ተሰግቷል
ዩክሬን በ48 ሰዓታት ውስጥ ከሩሲያ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር ጥሪ ማቅረቧ ተገለጸ፡፡
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር ጥሪ ያቀረበችው ሩስያ ጦሯን ወደ ዩክሬን ድንበር ማስጠጋቷንና በከሬሚያ ግዛት ማስፈሯን ተከትሎ በጊዜ ሂደት እየተባባሰ የመጣውን ወታደራዊ ፍጥጫ ለማብረድ በሚል መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
- ፕሬዝዳንት ባይደን የአሜሪካ ዜጎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ አሳስበዋል
- በዩክሬን ጉዳይ ሲወያዩ የነበሩት ሩሲያና እና አሜሪካ መግባባት አልቻሉም ተባለ
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ውይይት ቁልፍ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት እንዲሳተፉም ነው የጠየቀችው፡፡
ሞስኮ ለትንኮስ በሚመስል መልኩ እያደራጀችው ስላለው ጦር እንድታስረዳ በይፋ ብትጠየቅም እስካሁን የተሰጠ መልስ እንደሌለ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ ዲሚትሮ ኩሌባ ተናግሯል፡፡
ሚኒስትሩ ቀጣዩ እርምጃ በ48 ሰዓታት ውስጥ ስብሰባ ጠርቶ ሩሲያ ስላላት ዕቅድ "በግልፅ" ማውራት ነው ሲሉም ተደምጧል፡፡
ሞስኮ ዩክሬንን ለመውረር በሚመስል መልኩ ከ100 ሺህ የሚልቁ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ድንበር ማስጠጋቷ የተለያዩ ወቀሳዎች እያስተናገደች ትገኛለች፡፡
አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች ሲሉ፤ አሜሪካ ደግሞ ሞስኮ ወረራውን በአየር ጥቃት ልትከፍት ትችላለች ስትል አስጠንቅቃለች።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሃገራት ዜጎቻቸው ዩክሬንን ጥለው እንዲወጡ አሳስበዋል። አንዳንዶች ደግሞ የኤምባሲ ሠራተኞቻቸውን ከዋና ከተማዋ ኪዬቭ አሽሽተዋል።
ምእራባውያን ዩክሬን ባለው ጉዳይ ዜጎቻቸው በማስወጣት ረግድ በርካታ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ቢሆኑም ግን ችግሩ ይፈጠርባታል፤የተባለቸው ዩክሬን “ምንም የተለወጠ ነገር የለም ስለዚህም ማንም ሰው ሀገሪቱን ለቆ መውጣት የለበትም” እያለች ነው፡፡
የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ በጥቂት ቀናት ዩክሬንን ልትወር ነው የሚባለው “ማስረጃ የሌለው ወሬ ነው” ሲሉ አጣጥለዋል።
ሞስኮ በአንጻሩ ወረራ የሚባል ነገር በሀሳቤም የለም ስትል ተደምጣለች፡፡
የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ሀሰተኛ ዜና እያሰራጩ ህዝብ በማሸበር ላይ ተጠምዷል ስትልም ነው ሩሲያ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ አማካኝነት ከቀናት በፊት የገለጸችው፡፡
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጋር እሁድ ዕለት ቢያንስ ለአንድ ሰዓት የቆየ የስልክ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ባይደን ሀገራቸው ለዩክሬን ያላትን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ነግረዋቸዋል ሲሉ የዋይት ኃውስ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ቅዳሜ ለአንድ ሰዓት ያክል የስልክ ቆይታ እንዳደረጉ የተነገረላቸው ፕሬዝዳንት ባይደንና የሩሲያው አቻቸው ፑቲን ስምምነት ላይ ሳይደርሱ መቅረታቸው ተሰምቷል።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊከን የሩሲያ ጠብ አጫሪነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ቀደም ሲል መናገራቸው የሚታወስ ነው።
የሩሲያ ጥቃት በማንኛውም ቅጽበት ሊጀመር እንደሚችል በተለይም በፌብሩዋሪ 20 የኦሎምፒክ ፍጻሜ ዕለት ሊሆን እንደሚችል ምልክቶች ምልክቶች አሉ ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡
አሜሪካ ለዚህ ጥቃት ምላሽ 3 ሺህ የሠራዊት አባላትን ከኖርዝ ካሮላይና ቀጠና ወደ ፖላንድ አንቀሳቅሳለች፡፡ይሁንና እነዚህ ወታደሮች ከዩክሬን ወታደሮች ጋር ተሰልፈው ይዋጋሉ ወይስ አይዋጉም ለሚለው ግልጽ የሆነ ነገር የለም፡፡
የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው ሳምንት ጀምሮ፣ኪያቭ፣ ሞስኮና በርሊን ሲመላለሱ ነበር የሰነበቱት፡፡የማክሮን ወዲያ ወዲህ ማለት አይቀሬ ነው ለሚባለው ጦርነት የዲፕሎማሲ መፍትሄ ለመሻት እንደነበርም ይገለጻል፡፡