ከሩሲያ ጋር ፍጥጫ ውስጥ የገቡት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ፣ጆ ባይደን ወደ ኬቭ ጋበዙ
አሜሪካ፤ ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር አቅዳለች በሚል ሞስኮን መክሰሷ ይታወቃል
የአሜሪካና ዩክሬን ፕሬዝዳንቶች አንድ ሰዓት ገደማ በስልክ መነጋገራው ተሰምቷል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ፤የአሜሪካው አቻቸው ወደ ዩክሬን እንዲመጡ ግብዣ ማቅረባቸው ተሰምቷል።
ጆ ባይደን ወደ ኬቭ እንዲያቀኑ ግብዣ ያቀረቡት የዩክሬኑ አቻቸው ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር ውጥረት ውስጥ በገባችበት ወቅት መሆኑ የቀጠናውን ፖለቲካ ውጥረት ከፍ እንደሚያደርገው እየተነገረ ነው።
የአሜሪካ እና ዩክሬን ፕሬዝዳንቶች አንድ ሰዓት ሊሞላ 10 ደቂቃ ብቻ የጎደለው የስልክ ንግግር ካደረጉ በኋላ ባይደን ኬቭን እንዲጎበኙ ተጋብዘዋል፡፡
ባለፉት ሳምንታት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ 100 ሺህ ወታደሮችን ማስፈሯን አሜሪካ ገልጻ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ይህ ቁጥር 130 ሺ እንደደረሰ በይፋ አስታውቃለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ፤ የአሜሪካ አቻቸው በሚቀጥሉት ቀናት ሀገራቸውን እንዲጎበኙላቸው ጥሪ ያቀረቡት አካባቢዊ ውጥረቱ እንዲቀንስ መሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “የእርስዎ ጉብኝት አካባቢያዊ ጉዳዩን ለማርገብ ትልቅ ጠቀሜታ አለው” ሲሉ የአሜሪካ አቻቸው ሀገራቸውን እንዲጎበኙ ጠይቀዋል።
ሁለቱ መሪዎች ሰሞነኛውን የዩክሬንና የሩሲያ ጉዳይ ዋነኛ ጉዳያቸው እንደነበር ተገልጿል። አሜሪካ፣ ዩክሬን በሩሲያ ልትወረር ትችላለች የሚል ተደጋጋሚ መግለጫ እያሰማች ቢሆንም የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ግን መደናገጠ አያስፈልግም ሲሉ ከሳምንታት በፊት ተናግረው ነበር።
ሁለቱ መሪዎች አሁን ያለውን ውጥረት ለማርገብ አስቀድሞ አቅምን ማሳየት አሊያም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መነጋገር አስፈላጊ መሆናቸውን አንስተው ተወያይተዋል ተብሏል።
እስካሁን ባለው መረጃ ባይደን የአቻቸውን ግብዣ ተቀብለው ወደ ኬቭ ለማቅናት ስለመወሰናቸው የተነገረ ነገር የለም።