ብሊንከን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሊሾሙ ነው
ብሊንከን በኦባማ የአስተዳደር ዘመን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ምክትል የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ በመሆን ሰርተዋል
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሹመቱን ነገ ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል
ብሊንከን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሊሾሙ ነው
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የረጅም ጊዜ የውጭ ግንኙነት ልምድ ያላቸውን ዲፕሎማት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው ሊሾሙ መሆኑን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ፡፡
እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ ጆ ባይደን የሀርቫርድና የኮሎሚቢያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሩቅ የሆኑትን አንቶኒ ብሊንከንን ቀጣዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደሚሾሙ ይጠበቃል፡፡
ብሊንከን በባራክ ኦባማ የአስተዳደር ዘመን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ምክትል የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ በመሆን ሰርተዋል፡፡ የጆ ባይደንም የቅርብ ሰው ናቸው፡፡
ለዓለም አቀፍ ትብብር ጠበቃ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ብሊንከን አሜሪካን ትታው ወደ ወጣችው የፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት እና ወደ ኢራኑ የኒዩክለር ስምምነት እንደሚመልሷት ይጠበቃል እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ፡፡
ሮይተርስ የብሊንከን ሹመት ነገ ይፋ ሊሆን እንደሚችል አስነብቧል፡፡
ተሿሚው በዓለም ላይ ላሉ ችግሮች መፍትሄው የተናጠል ሩጫ ሳይሆን ትብብር ነው ብለው እንደሚያምኑ ይነገራል፡፡
ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎችንም መግታት የሚቻለው በጋራ በሚገኙ መፍትሄዎች ነው የሚል አቋምን እንደሚያራምዱም ነው የሚነገረው፡፡
በ2015 የኒክለር ስምምነት ወቅት ስምምነቱን በቅርብ ከሚከታተሉት ሰዎች መካከል አንዱ የነበሩት ቀጣዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶናልድ ትራምፕ ዋሸንግተን ከዚህ ስምምነት እንዲትወጣ ሲያደርጉ ተቃውመው ነበር፡፡
ከብሊንከን በተጨማሪም ባይደን ጃክ ሱሊቫንን ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ፣ ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር አድርገው እንደሚሾሙ ይጠበቃል፡፡
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩት ሱዛን ራይስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የቀድሞዋ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የ2016 የዴሞክራቶች ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ሂላሪ ክሊንተን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው በባይደን ሊሾሙ እንደሚችሉ ተገምቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡