አለልኝ ከአምባሳደር በላይነሽ ዘቫዲያ ቀጥሎ በኢትዮጵያ አምባሳደርነት የተሾሙ ሁለተኛው ቤተ እስራኤላዊ ናቸው
አለልኝ አድማሱ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ሆነው ተሾሙ
እስራኤል አለልኝ አድማሱን የኢትዮጵያ አምባሳደር አድርጋ መሾሟ ተሰምቷል፡፡
የቀድሞው የእስራኤል ፓርላማ (ክኔሴት) አባል አለልኝ አድማሱ ራፋኤል ሞራቭን በመተካት ነው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋቢ አሽኬናዚ በአምባሳደርነት የተሾሙት፡፡
በእስራኤል የሚገኘው “ካአን ሬካ” የአማርኛ ሬዲዮ ጣቢያም ስለ ሹመቱ ዘግቧል፡፡
በቤተ እስራኤላውያን ዘንድ በስፋት የሚታወቁት አለልኝ በቤተ እስራኤላውያኑ ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያ አማካሪ ነበሩ፡፡
በሹመቱ መደሰታቸውን የገለጹት የኢሚግሬሽን እና የውህደት ሚኒስትሯ ፕኒና ታመነ አለልኝ ለቤተ እስራኤላውያኑ ብዙ መስራታቸውን በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠንከር የሚችሉ ዲፕሎማት ይሆናሉ የሚል ትልቅ እምነት እንዳላቸውም አስፍረዋል፡፡
አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ እ.ኤ.አ ከ2017 ጀምሮ ያለፉትን 4 ዓመታት በአዲስ አበባ አሳልፈዋል፡፡
አለልኝ አድማሱ እስራኤልን ወክለው በአምባሳደርነት የተሾሙ ሁለተኛው ቤተ እስራኤላዊ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት በላይነሽ ዘቫዲያ ከአሁን ቀደም (ከ2004 እስከ 2009 ዓ/ም) በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ሆነው ማገልገላቸው የሚታወስ ነው፡፡
የአለልኝ ሹመት የሃገራቱ የቀደመ እና በደም የተሳሰረ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲውን ያጠብቃል፡፡
በሃገራቱ መንግስታት መካከል ቤተ እስራኤላውያኑን ከኢትዮጵያ ለመውሰድ የተጀመረውን ጥረት ከግብ ለማድረስም ያስችላል፡፡
ተጨማሪ 2 ሺ ገደማ ቤተ እስራኤላውያን በቅርቡ ወደዚያው ያመራሉ መባሉ የሚታወስ ነው፡፡
ባሳለፍነው ወርሃ ግንቦት 119 ቤተ እስራኤላውያን ወደዚያው ማምራታቸውም አይዘነጋም፡፡
በሹመቱ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞች ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖዎች ሊገኙበት እንደሚችሉም ይጠበቃል፡፡
ቤተ እስራኤላውያኑ በታላላቅ የመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱንም የሚያሳይ ነው፡፡
ከአሁን ቀደም ፕኒና ታመነ በኢሚግሬሽን እና ውህደት ሚኒስትርነት ጋዲ ይባርከን በምክትል የደህንነት ሚኒስትርነት መሾማቸው ይታወሳል፡፡
በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩት ጋዲ ይባርከን ለገበታ ለሃገር ፕሮጄክቶች የበኩላቸውን ማበርከታቸውንና ቤተ እስራኤላውያኑን ለማስተባበር ቃል መግባታቸውም አይዘነጋም፡፡
የበርሃ አንበጣ መንጋ የመከላከል ስራውን የሚያግዙ የእስራኤል ባለሙያዎች ከሰሞኑም አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡