የአሜሪከ ኮንግረስ የባይደንን አሸናፊነት አጸደቀ
“በውጤቱ ሙሉ በሙሉ ባላምንም ጥር 20 ላይ ሥርዓት ባለው መንገድ የሥልጣን ሽግግር ይኖራል” ዶ. ትራምፕ
“በውጤቱ ሙሉ በሙሉ ባላምንም ጥር 20 ላይ ሥርዓት ባለው መንገድ የሥልጣን ሽግግር ይኖራል” ዶ. ትራምፕ
እሰጥ አገባዎች የበዙበት የአሜሪካ ምርጫ የመጨረሻ ውሳኔውን አግኝቷል፡፡ የዴሞክራቶቹ እጮ ጆ ባይደን 306 የውክልና ድምጽ ስለማግኘታቸው እና ተቀናቃኛቸው እና ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ 232 ድምጽ ስለማግኘታቸው ኮንግረሱ የመጨረሻ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዚህም መሰረት ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን በአውሮፓውያኑ ጥር 20 የነጩን ቤተ መንግሥት ቁልፍ ከትራምፕ ይረከባሉ፡፡ ካማላ ሀሪስ ደግሞ ምክትላቸው ናቸው፡፡
ሽንፈታቸው ያልተዋጠላቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ 5 ግዛቶች ላይ ድምጽ ተጭበርብሯል በሚል ያቀረቧቸው ክሶች ሁሉ ውድቅ ከተደረገባቸው በኋላ ፣ እንደመጨረሻ አማራጭ የባይደንን ድል ለማጽደቅ ኮንግረሱ የሚያደርገውን ስብሰባ እንዲያውኩ ደጋፊዎቻቸውን አሰማርተዋል፡፡ በዚህም የ 4 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች ካፒቶል ሂል በመባል የሚታወቀውን የኮንግረሱን መሰብሰቢያ ሰብረው በመግባት ፣ ሂደቱን ለጥቂት ሰዓታት ካስተጓጎሉ በኋላ ፖሊስ አመጹን ተቆጣጥሮ ነው ሰብሰባው የቀጠለው፡፡
በስብሰባው ከየግዛቱ የተወሰኑ ሰዎች የሰጡት የኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ ተቆጥሮ የመጨረሻው ውጤት በኮንግረሱ ጸድቋል፡፡ ስብሰባውን የመሩት ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ሁሉም ነገር መጠናቀቁን ገልጸው “ወደ ስራችን እንመለስ” ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደግሞ “በተደጋጋሚ ሕጋዊ ድምጾች ብቻ የተቆጠሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ትግላችንን እንቀጥላለን ብለናል፡፡ የኮንግረሱ ውሳኔ በፕሬዚዳንታዊ ታሪክ ውስጥ ታላቁ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን የሚያበቃበት ቢሆንም ቆይታችን አሜሪካን ዳግም ታላቅ ለማድረግ የትግላችን መጀመሪያ ነበር” ማለታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
“ምንም እንኳን በምርጫው ውጤት ሙሉ በሙሉ ባላምንም ጥር 20 ላይ ሥርዓት ባለው መንገድ የሥልጣን ሽግግር ይኖራል” ሲሉም የኮንግረሱን ውሳኔ ተከትሎ ባሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ፕሬዝዳንቱ ለአመጽ የወጡ ደጋፊዎቻቸውን እወዳችኋለሁ ማለታቸውን እና ሌሎች አመጽ ቀስቃሽ ትሁፎችን መለጠፋቸውን ተከትሎ ፣ ትዊተር ፣ ፌስቡክ ፣ ኢኒስታግራም እና ዩ ቲዩብ የፕሬዝዳንቱን ገጾች አግደዋል፡፡
ትዊተር ፕሬዝዳንቱ ከኩባንያው ሕግ የሚጻረሩ ጽሁፎቻቸውን እስካላጠፉ ገጻቸው ተዘግቶ እንደሚቆይ አስታውቋል፡፡ ፌስቡክ እና ኢኒስታግራም ደግሞ የ24 ሰዓት እገዳ ጥለውባቸዋል፡፡ ዩቲዩብም የለጠፉትን ቪዲዮ አጥፍቷል፡፡