የባይደን አለምአቀፋዊ ተቀባይነት ከትራምፕ የተሻለ መሆኑን ጥናት አመላከተ
ከ34 ሀገራት የተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች ከትራምፕ ይልቅ የባይደንን በፕሬዝዳንትነት መዝለቅ የሚፈልጉ ናቸው
በአንጻሩ ሁለቱ ተፎካካሪዎች በአሜሪካ ባላቸው ተቀባይነት ደረጃ ትራምፕ ከባይደን የተሻለ ተቀባይነትን አግኝተዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዶናልድ ትራምፕ የተሻለ አለምአቀፋዊ ተቀባይነት እንዳላቸው ከህዝብ የተሰበሰበ አስተያየትን መሰረት አድርጎ የተሰራ ጥናት ጠቁሟል፡፡
ፒው በተሰኘው የጥናት ማዕከል በ34 ሀገራት የተሰራው ጥናት ባይደን ከትራም የተሻለ ተቀባይነት እንዳላቸው ነው ያመለከተው፡፡
ከጥር 5 እስከ ግንቦት 21 የተካሄደው ጥናቱ 40 ሺህ 566 ሰዎች የተሳተፉበት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 43 በመቶዎቹ ባይደን በስልጣን ላይ ቢቆዩ እንደሚመርጡ ሀሳባቸውን ሲሰጡ 28 በመቶዎቹ ደግሞ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ወደ ስልጣን መመለስ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
በ24 ሀገራት ባይደን ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ ሲሆን በ21ዱ ሀገራት ደግሞ ከባለፈው አመት አንጻር እጅግ ዝቅተኛ ድጋፍ አግኝተዋል። ሃንጋሪ እና ቱኒዝያን በመሳሰሉ ሀገራት የትራምፕ ድጋፍ ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡
በአንጸሩ ሁለቱ የ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪዎች በሀገር ቤት ያላቸው ተቀባይነት የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ሮይተርስ ያሰባሰበው የህዝብ አስተያየት ባይደን 30 በመቶ ትራምፕ ደግሞ በ40 በመቶ አሜሪካዊያን ዘንድ ተቀባይነት እንዳላቸው የሚያመላክት ነው፡፡
በሁለት አመት ውስጥ ዝቅተኛ የተባለውን ተቀባይነት ያገኙት ጆባይደን በመጪው ምርጫ ላይ በሚኖራቸው ድጋፍ ላይ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል ተነግሯል፡፡
23 በመቶ ድምጽ ሰጪዎች የአሜሪካ ኢኮኖሚ እየሄደበት ያለው መንገድ ትክክል አለመሆኑን ሲናገሩ 13 በመቶዎቹ የባይደን አስተዳደደር በስደተኞች ጉዳይ የሚከተለው ፖሊስ ፕሬዝዳንቱን የማይደግፉበት ምክንያት እንደሆነ አስቀምጠዋል፡፡
40 በመቶ ድምጽ ሰጪዎች ትራምፕ ከባይደን የተሻለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደነበራቸው ሲናገሩ 42 በመቶዎቹ ደግሞ በስደተኞች ፖሊሲ ዙሪያ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት አካሄድ እንደሚመርጡ ተናግረዋል፡፡
ሮይተርስ ሁለቱን ወገኖች ካወዳደረባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ አለም አቀፋዊ ግጭቶች እና ጂኦፖለቲክሳዊ ውጥረቶችን የተመለከተ ሲሆን በዚህም ዙርያ ትራምፕ ከባይደን የተሻለ የአሜሪካዊያን ድጋፍን አግኝተዋል፡፡
36 በመቶ ድምጽ ሰጪዎች ትራምፕ አለምአቀፍ ግጭቶችን እና ሽብርተኝነትን በመቆጣጠር ረገድ የተሻሉ ናቸው ሲሉ ጆባይደን ያገኙት ድምጽ 29 በመቶ ነው፡፡
እነኚህ ከህዝብ የተሰበሰቡ ድምጾች የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመከናወኑ በፊት አሸናፊውን ለመተንበይ ለትንታኔ የሚውሉ ናቸው፡፡
እጩዎቹ በአለም አቀፍ ደረጃ እና በሀገር ውስጥ በሚነሱ አንገብጋቢ ጉዳዮች በሚከተሏቸው ፖሊሲዎች ላይ ያላቸው ተቀባይነት በምርጫ ቅስቀሳቸው ውስጥ አካተው የሚጠቀሙበት ሲሆን አጠቃላይ የህዝቡንም የልብ ትርታ ለማድመጥ የሚያግዛቸው ነው፡፡