ተጠባቂው የባይደን እና የትራምፕ የምርጫ ክርክር ምን ምን ጉዳዮችን ይዟል?
ሁለቱ እጩዎች በዩክሬን እና በጋዛ ጦርነት እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ላይ ትኩረት አድርገው ይከራከራሉ
ከፖሊሲያዊ ጉዳዮች ባለፈ ባይደን እና ትራምፕ በግል ጉዳዮቻቸው ላይ የሚሰነዛዘሯቸው ነቀፌታዎች ክርክሩን ተጠባቂ አድርጎታል
የ2024 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ክርክር በሚቀጥለው ሳምንት በአትላንታ ይከናወናል። በሲኤንኤን አዘጋጅነት የሚደረገው ክርክር ከወዲሁ ከፍተኛ ትኩረትን አግኝቷል፡፡
ሁለቱ እጩዎች በየግላቸው ከፖሊሲ አውጪዎች እና አማካሪዎች ጋር ለክርክሩ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን በፖሊሲያዊ ጉዳዮች ፣ ፕሬዝዳንት ቢሆኑ ስለሚከተሏቸው አሰራሮች እንዲሁም በአለም አቀፍ ጂኦፖለቲክሳዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የሚከራከሩ ይሆናል፡፡
በ2020 ምርጫ ክርክር ላይ በግል ጉዳዮች ላይ በአብዘሀኛው ሲጎነታተሉ እና ያለ መደማመጥ ሲያወሩ የታዩት ተፎካካሪዎቹ በዘንድሮው ምርጫ የሚያወራው ሰው ሀሳቡን እስኪጨርስ ድረስ ማይክ ለማጥፋት ተስማምተዋል፡፡
በሁለቱ ሰዎች መካከል ባለፉት አራት አመታት የታየው የቃላት ጦርነት ይህን ክርክር እንዲጠበቁ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው። ከዚህ ባለፈ ግን ጠንከር ባሉ ፖሊሲያዊ ጉዳዮች ላይ አጀንዳቸውን የሚያስተዋውቁ ይሆናል፡፡
ከነዚህ ጉዳዮች መካከል ህገ ወጥ ስደተኞችን የሚመለከተው አጀንዳ ይጠቀሳል። የዴሞክራት እጩው ባይደን በስደተኞች ዙርያ ትራምፕ በስልጣን ላይ በነበሩበት ግዜ ጠበቅ አድርገውት የነበሩትን ፖሊሲ አላልተዋል፡፡
ቅድሚያ ለአሜሪካዊያን በሚል መፈክራቸው የሚታወቁት የቀድሞው ፕሬዝዳነት በበኩላቸው በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ህገወጥ ስደተኞችን ለመከላከል በሜክሲኮ በኩል ግንብ ለማስገንባት እቅድ አውጥተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሜሪካ ውስጥ እየበረከተ ላለው ወንጀል እና ህገወጥ ድርጊቶች ስደተኞች ተጠያቂ ናቸው የሚል እምነት ያላቸው ትራምፕ በርካታ ህገወጥ ስደተኞችን ወደ መጡበት መልሰዋል፡፡ በዚህም ሁለቱ እጩዎች በዚህ ጉዳይ ባላቸው የተለያየ አተያይ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን እንደሚለዋወጡ ይጠበቃል፡፡
ሌላው የዩክሬን እና የጋዛ ጦርነትን የተመለከተው ጉዳይ ነው። ትራምፕ እኔ በስልጣን ላይ ብኖር ኖሮ ሩሲያ ዩክሬንን አትወርም፤ የጋዛውም ጦርነት አይከሰትም ነበር ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡
ባይደን አሜሪካን እና አለምን የመሩበት መንገድ ደካማ መሆን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል ሲሉም ይወቅሳሉ። ትራምፕ አክለውም ጆባይደን በስልጣን የሚቀጥሉ ከሆነ ሶስተኛው የአለም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል አስጠንቅቀዋል፡፡
በሩስያ ዩክሬን ጦርነት ለዘለንስኪ አስተዳደር በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ድጋፍ ያደረጉት ባይደን በበኩላቸው የትራምፕ እና ፑቲን ግንኙነት የአሜሪካን ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው በሚል ይከራከራሉ፡፡
ኢኮኖሚን በተመለከተ የባንኮች ወለድ መጨመር፣ የዋጋ ንረት እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ላይ ይከራከራሉ፡፡
የአሜሪካዊያን ኩባንያዎች የአዕምሮ መብት ጥበቃ እና ከቻይና ጋር ያለ የንግድ ግንኙነት በተጨማሪ የሚነሱ ሀሳቦች ናቸው፡፡
የግል ጉዳዮችን በተመለከተ ሁለቱ እጩዎች ይጎነታተሉባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ሀሳቦች መካከል የባይደን የእድሜ ሁኔታ እና የትራምፕ የወንጀል ክስ ጥፋተኝነት ይጠበቃሉ፡፡
የ81 አመቱ ባይደን የሚገኙበት አድሜ አሜሪካን የሚያክል ጥልቅ ሀገር ለመምራት የሚያስቻለቸው ሳይሆን በአረጋውያን መቆያ እንዲቀመጡ የሚያስገድዳቸው ነው በማለት በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ሲሳለቁ የነበሩት ትራምፕ ባይደን መነጋገርያ የሆኑባቸውን ስህተቶች በማንሳት ለፕሬዝዳንትነት ብቁ አለመሆናቸውን ሊያስተጋቡ ይችላሉ፡፡
የዴሞክራቱ እጩ አሁናዊው ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ትራምፕ ጥፋተኛ የተባሉባቸውን የወንጀል ክሶች በማንሳት የማይታመኑ ሰው ስለመሆናቸው ሊናገሩ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሁለቱም እጩዎች ከፖሊሲ አውጭዎች ጋር ለክክክሩ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በካምፕ ዴቪድ የሚገኙት ባይደን ከትራምፕ ሊሰነዘርባቸው ለሚችል ነቀፌታ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ ዝግጅት እያደረጉ ነው ተብሏል፡፡
ትራምፕ ከተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ጋር በሚያደርጉት ቃለ ምልልስ እና በምርጫ ቅስቀሳዎች ወቅት የሚቀርብላቸውን ጥያቄ በመመለስ ባገኙት ልምድ በክርክሩ ቅድመ ግምትን አግኝተዋል፡፡
በመጪው ሳምንት ሃሙስ በአትላንታ ሴኤንኤን ስቱዲዮ የሚደረገው ክርክር ያለተመልካች በዝግ ስቱድዮ የሚከናወን ይሆናል፡፡