ፕሬዝዳንት ባይደንና የቻይና ሺ ጂንፒንግ በታይዋን እና በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ጉዳይ ይወያያሉ
በታይዋን ጉዳይ አለመግባባት ውስጥ ያሉት የአሜሪካ እና ቻይና ፕሬዝዳንቶች ውይይት ሊያደርጉ መሆኑ ተገለጸ።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና አቻቸው ሺ ጂንፒንግ በታይዋን እና በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ላይ ትኩረት ያደረገ ንግግር እንደሚያደርጉም ነው የተገለጸው፡፡
ሁለቱ መሪዎች ነገ ከአራት ወራት በኋላ በስልክ ንግግር እንደሚደርጉ አንድ ከፍተኛ የዋሸንግተን ባለስልጣን መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካዋ አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ከሰሞኑ ታይዋንን እንደሚጎበኙ መግለጻቸውን ተከትሎ ቤጅንግ ቁጣዋን ገልጻለች፡፡
ከዚህ ባለፈም ቻይና አፈጉባዔዋ ወደ ታይዋን የሚሄዱ ካልሆነ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል አስጠንቅቃ ነበር፡፡
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የስልክ ውይይት ያደርጋሉ የተባለው በዚህ ውጥረት ውስጥም ሆነው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የመሪዎቹን የስልክ ንግግር አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበለት የቻይና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
ምንም እንኳን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና አቻቸው ሺ ጂንፒንግ በታይዋን ጉዳይ ላይ ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚወያዩ ቢጠበቅም በአውሮፓ ያለው ወታደራዊ ሁኔታም የውይይታቸው አካል እንደሚሆን ተገምቷል፡፡
መሪዎቹ በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ላይ ትኩረት ያደረገ ንግግር ይኖራቸዋል ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን በእስካሁኑ ሂደት ዋሸንግተን ከዩክሬን፤ ቤጅንግ ደግሞ ከሩሲያ ጎን መሆናቸው ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ የደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፤ ሁለቱ መሪዎች በኢኮኖሚ ውድድር ላይም ይነጋገራሉ ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን ከቻይናው አቻቸው ጋር ነገ ውይይት የሚያደርጉት ከኮሮና ቫይረስ ካገገሙ በኋላ ነው፡፡