ቻይና በታይዋን ጉዳይ ለአሜሪካ ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጠች
ቻይና ታይዋንን ለመነጠል ለሚደረግ ሙከራ ጦሯ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፍል ዝግጁ መሆኑን አስታውቃለች
የቻይና መከላከያ ሚ/ር “ታይዋንን ለመነጠል የሚደረግ እንቅስቃሴ ወደ ጦርነት የስገባናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል
ቻይና በታይዋን ጉዳይ እንደማትደራደርና ውጊያ መግጠም ካለባትም ለመግጠም ዝግጁ መሆኗን በመግለፅ ቤጂንግ አሜሪካን አስጠንቅቃለች።
የቻይና የመከላከያ ሚኒስትር ዌዪ ፈንጊሄ ከአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሎልዩድ አውስቲን ጋር ከኢስያ የደህንነት ጉባዔ ጎን ለጎን ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅትም የቻይናው መከላከያ ሚኒስትር ዌዪ ፈንጊሄ፤ ታይዋንን ከቻይና መገንጠል የቻይና ወታደር “ማንኛውንም አይነት ዋጋ በመክፈል ከመዋጋት ውጭ ምርጫ እንዳይኖረው ያደርጋል” ብለዋል።
“ሕዝባዊ ነፃ አውጪ ጦር” በመባል የሚጠራው የቻይና ጦር የሀገሩን ብሔራዊ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ከማስጠበቅ በቀር ሌላ ምርጫ እንደማይኖረውም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎልዩድ አውስቲን በበኩላቸው “ቻይና በታይዋን አካባቢ የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ግጭት ቀስቃሽ አለመረጋጋትን የሚፈጥሩ ናቸው” ማለታቸው ተሰምቷል።
የቻይና የጦር አውሮፐላኖች በየቀኑ በታይዋን ደሴት አካባቢ የሚያደርጉት በረራዎች እና እንቅስቃሴዎች የቸካባውን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ አክለውም፤ ቤጂንግ የቻይና ብቸኛ መንግስት መሆኗን አሜሪካ እንደምትቀበል እና ይህንን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል።
ቤጅንግ በተደጋጋሚ ፤ ታይዋን ነጻነቷን ከማወጅ እንድትቆጠብ የሚያስጠነቅቅ መልዕክት ስታስተላልፍ የቆየች ሲሆን የአሁኑ ግን ቀጥተኛ ነው ተብሏል።
ቻይና ይህንን መልዕክት ያስተላለፈችው አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ ተደጋጋሚ አስተያየት መስጠቷን ተከትሎ ነው።
ቻይና በታይዋን ላይ ወረራ ከፈጸመች፤ አሜሪካ ወታደራዊ አጸፋ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መናራቸውም የሚታወስ ነው።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጅንፒንግ ከወራት በፊት ታይዋንን ከቻይና ጋር ለማዋሃድ መዛታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ ለማዋሃድ ኃይል መጠቀም ስለማሰባቸው አልተናገሩም።
ታይዋን ነጻ ሀገር ነኝ የምትል ሲሆን፤ በአንጻሩ ታይዋንን የግዛቷ አካል አድርጋ ትመለከታታለች።