የአሜሪካዋ አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ቻይና አስጠነቀቀች
ናንሲ ፔሎሲ ነሀሴ ወር ላይ ታይዋንን የመጎብኘት እቅድ አውጥተዋል
ቻይና ፔሎሲ ታይዋንን ከጎበኙ ወታደራዊ ጨምሮ ማንኛውንም አይነት እርምጃ ልወስድ እችላለሁ ስትል አስጠንቅቃለች
አፈጉባኤዋ ናንሴ ፔሎሲ የፊታችን ነሀሴ ወር ላይ ታይዋንን እንደሚጎበኙ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል አዲስ አለመግባባት ተከስቷል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛኦ ሊጃን ለፋይናንሺያን ታየምስ እንዳሉት “ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ ቻይና ወታደራዊ እርምጃዎችን ጨምሮ ማንኛውንን አይነት እርምጃ ለመውሰድ በሚገባ ተዘጋጅታለች” ብለዋል፡፡
"አሜሪካ አሁን በያዘችው እቅድ የምትመራ ከሆነም ቻይና ጠንካራ እርምጃ መውሰዷን ትቀጥላለች ፣ለሚፈጠረው ክስተትም አሜሪካ ሃላፊነቱን ትወስዳለች” ሱሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡
የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት እስካሁን ቻይና ስለሰጠችው ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ምንም ያላለ ሲሆን በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው ራሳቸውን ያገለሉት ፕሬዝዳንት ባይደን በያዝነው ሳምንት ውስጥ ከቻይና አቻቸው ሺ ሺፒንግ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል ሲሉ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቻይና ታይዋን የግዛቴ አንድ አካል እንጂ ሀገር አይደለችም በሚል ጠንካራ አቋም ያላት ሲሆን ታይዋን ይሄንን እንድትቀበል የተለያዩ ጫናዎችን በማድረስ ላይ እንደሆነች ይጠቀሳል፡፡
የታይዋን መንግስት በበኩሉ ጉዳዩ የ23 ሚሊዮን ዜጎች ውሳኔ እንጂ የቻይና ማዕከላዊ መንግስት አይደለም በሀይል ከተጠቃንም ሁላችንም ለሉዓላዊነታችን እንዋጋለን በማለት ላይ ትገኛለች፡፡