ባይደን እና ሺ የፊታችን ረቡዕ በሳንፍራንሲስኮ ይወያያሉ
መሪዎቹ ከአንድ አመት በኋላ ፊት ለፊት የሚያደርጉት ምክክር የልዕለ ሃያላኑን ሀገራት ቅራኔ እንደሚያለዝብ ይጠበቃል
የእስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከቻይና አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ጋር የፊታችን ረቡዕ በሳንፍራንሲስኮ እንደሚወያዩ ተገለጸ።
መሪዎቹ ከህዳር 2022 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የሚመክሩት ከእስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ጎን ለጎን ነው።
ምክክሩ ከሩሲያ-ዩክሬን እስከ እስራኤል-ሃማስ ጦርነት የተለያዩ አለማቀፍ ጉዳዮችን ይዳስሳል ተብሏል።
የታይዋን ጉዳይ፣ ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር የፈጠረችው ጥብቅ ግንኙነት፣ የኢንዶ ፓስፊክ ቀጠና ውጥረት፣ የቤጂንግ የሰብአዊ መብት አያያዝ እና የንግድ ፉክክር በሳንፍራንሲስኮው ውይይት የሚነሱ ነጥቦች መሆናቸውንም ዋይትሃውስ አስታውቋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ በአሜሪካ የአራት ቀናት ቆይታ እንደሚያደርጉና ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር እንደሚመክሩ አረጋግጧል።
ከአስር አመት በላይ ትውውቅ ያላቸው ባይደን እና ሺ ከ2021 ወዲህ ስድስት ጊዜ ተገናኝተው መክረዋል።
ይሁን እንጂ በንግድ ፉክክር ኢፍትሃዊነት እና በታይዋን ጉዳይ የገቡበት ሰጣ ገባ መሪዎቹን ባላንጣ ካስመሰላቸው አመታት ተቆጥረዋል።
መሪዎቹ ለውይይት ሲቀመጡም እርስ በርስ በመጠራጠር ነው የሚለው ሬውተርስ፥ የሳንፍራንሲስኮው ውይይት ቅራኔያቸውን ያለዝቡበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘግቧል።
ከሞስኮ እና ፒዮንግያንግ ጋር ግንኙነቷን ያጠናከረችው ቤጂንግ ከዋሽንግተን ጋር ልዩነቷን ባሰፉ ጉዳዮች ዙሪያ ለስአታት ምክክር እንደሚደረግ ነው ያስታወቀው።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት በኢራን ተሳትፎ ምክንያት አድማሱን እንዳያሰፋም ሺ በቴህራን ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ባይደን ጥሪ ያቀርባሉ ተብሏል።
ቻይና በበኩሏ እንደ ሉአላዊ ግዛቷ ለምትመለከታት ታይዋን ከአሜሪካ እየተደረገ የሚገኘው ወታደራዊ ድጋፍ እንዲቆም ታሳስባለች ተብሎ ይጠበቃል።
በታይዋን ሰርጥ፣ በደቡባዊ እና ምስራቅ ቻይና ባህር የጎረቤቶቿ እንቅስቃሴ ያሰጋት ቤጂንግ በኢንዶ ፓስፊክ ቀጠና የዋሽንግተን ድርሻ ምን መሆን እንዳለበት በምክክሩ ግልጽ አቋሟን እንደምታንጸባርቅም ነው የሚጠበቀው።
ጂንፒንግ በእስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ላይም የሀገራቸውን ስጋት እንደሚገልጹ ይጠበቃል።