በስም ያልተጠቀሰ ተጠርጣሪ በመከላከያ ተቋም ውስጥ ይሰራ ነበር ተብሏል
የቻይና ከፍተኛ የስለላ ድርጅት በመከላከያ ተቋሙ ውስጥ ይሰራ የነበረን አንድ የቻይና ዜጋ ለአሜሪካ በመሰለል መክሰሱን አስታውቋል።
ድርጅቱ የክሱ መዝገብ በደቡብ ምዕራብ ቼንግዱ ከተማ ፍርድ ቤት መተላለፉን ተናግሯል።
ክሱ ቤጂንግ ለብሄራዊ ደህንነት ያላትን ከፍተኛ ቁርጠኝነት እያሳየች ባለችበት ወቅት የመጣ ነው።
ሀገሪቱ የጸረ-ስለላ ህጎቿን እና የሀገር ውስጥ ሙስናዎችን ለመቆጣጠር ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው።
የቻይና መንግስት መገናኛ ብዙኻን እንደዘገበው ሁው የተባው ተጠርጣሪ በስም ያልተጠቀሰ የመከላከያ ተቋም ውስጥ ይሰራ ነበር።
በፈረንጆቹ 2013 በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ጎብኝ መምህር ሆኖ የቻይናን መንግስት ሚስጥር እንዲያወጣ መገደዱ ተገልጿል።
ለተጠርጣሪው ቅርብ የሆነ የአሜሪካ ፕሮፌሰር የአማካሪ ድርጅት ሰራተኛ ነኝ ከሚል ሰው ጋር እንዳስተዋወቀው ተጠቅሷል።
ግለሰቡ ኩባንያውን ሽፋን አድርጎ የሚጠቀም አሜሪካዊ “የደህንነት ኦፊሰር” ነበር ሲል ዘገባው ገልጿል።
በቀጣዮቹ ወራትም "ሰላዩ" የኩባንያው አማካሪ እንዲሆን በማግባባት ለአገልግሎቱ ክፍያም በእያንዳንዱ ቀጠሮ ከ600 እስከ 700 ዶላር እንደሚከፈለው ቃል ገብቶለታልም ተብሏል።
ተጠርጣሪው ለአንድ በሰዓት በሚፈጅ ጊዜ ውስጥ ሚስጥራዊ ጉዳዮችን እንዲገልጽ ይጠየቅ ነበር የተባለ ሲሆን፤ ለዚህም አንድ ሽህ ዶላር እንደ ክፍያ ያገኛል ሲል ዘገባው ገልጿል።
ሁው በ2014 ወደ ቻይና ከተመለሰ በኋላም ትብብሩ ቀጥሏል ተብሏል።
ግለሰቡ በራሱ ተነሳሽነት የሀገር መከላከያ እና የወታደራዊ ኢንደስትሪ ዘርፍ የስለላ መረጃዎችን መስጠቱንም ዘገባው አመልክቷል።