ፕሬዝዳንት ፑቲን ወታደራዊ እና የንግድ ተቋማት መሪዎችን አስከትለው ወደ ቤጂንግ ያቀናሉ ተብሏል
ፕሬዝዳንት ፑቲን ቻይናን እንደሚጎበኙ አስታወቁ፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በያዝነው ሳምንት ወደ ቤጂንግ እንደሚያቀኑ ተገልጿል፡፡
ቻይና የፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ የቤልት ኤንድ ሮድ ጉባኤን በቤጂንግ የምታስተናግድ ሲሆን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን የዚህ ጉባኤ የክብር እንግዳ እንደሚሆኑ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቻይና እና ሩሲያ አሁን ያለው የዓለም ስርዓት ሚዛናዊ ያልሆነ እና የአንድ ወገን የበላይነት ያለበት ነው በሚል አዲስ ዓለም ስርዓትን ለመፍጠር እየሰሩ ካሉ ጥቂት የዓለማችን ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ሁለቱ ሀገራት በመካከላቸው ገደብ አልባ ወዳጅነትን መመስረታቸውን ያስታወቁ ሲሆን የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ከሁለት ወራት በፊት ሩሲያን ጎብኝተዋል፡፡
አሁን ደግሞ ፕሬዝዳንት ፑቲን ወደ ቤጂንግ አቅንትው ከቻይና አቻቸው ጋር በወታደራዊ፣ ንግድ እና ሌሎች የትብብር መስኮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን ወደ ቤጂንግ የሚያቀኑት ወታደራዊ እና የንግድ ተቋማት መሪዎችን እና ባለሙያዎችን አስከትለው ነው ተብሏል፡፡
ቻይና በምዕራባዊያን ሀገራት ማዕቀብ የተጣለባቸውን ሀገራት ነዳጅ በመግዛት ቀዳሚ ሀገር ናት የተባለ ሲሆን ይህም ርካሽ ነዳጅ እንድተገዛ አድርጓታል፡፡
በዚህም መሰረት ቻይና በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 10 ቢሊዮን ዶላር አትርፋለች የተባለ ሲሆን ሩሲያ፣ ኢራን እና ቬንዙዌላ ደግሞ ነዳጃቸውን በርካሽ ለቻይና የሸጡ ሀገራት ናቸው፡፡
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የሚያደርጓቸው ትብብሮች በዋሸንግተን በጥርጣሬ የሚታዩ ሲሆን የሀገራቱ ተጨማሪ ትብብሮች በአሜሪካ በስጋትነት የሚታዩ ነውም ተብሏል፡፡
18 ትሪሊዮን ዶላር ዓመታዊ ኢኮኖሚ ያላት ቻይና 27 ትሪሊዮን ዓመታዊ ኢኮኖሚ ያላት አሜሪካንን ለመገዳደር ሩሲያ ዋነኛ አጋሯ ሆናለች፡፡
ቻይና የዓለማችንን ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካንን ለመገዳደር በቴክኖሎጂ፣ ጠፈር ሳይንስ፣ ወታደራዊ ሀይል እና ሌሎች መስኮች ብልጫ ለመውሰድ እንደ ሩሲያ ካሉ ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር በማሳደግ ላይ መሆኗም ተገልጿል፡፡