የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከጦርነት ቢሊየን ዶላሮችን እንደሚያተርፉ ሪፖርት አመላከተ
አማዞን፣ ፌስቡክ፣ ጉግል፣ ማይክሮሶፍትና ትዊተር በጦርነት ላይ ያተኮሩ ትላልቅ ኮንትራቶችን ከመንግስት ወስደው ሲሰሩ ነበር
የአሜሪከ መንግስት ከ2004 አንስቶ ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር ባደረገው ስምምነት 43.8 ቢሊየን ዶላር ወጪን አድርጓል
ታላላቅ የአሜሪካን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ሀገሪቱ የመስከረም 11ዱን ሽብር ጥቃት ተከትሎ ከመጣውና አሜሪካን ሽብርተኝነትን የመዋጋት (War On Terror) ብላ ከሰየመችው ጦርነት በርካታ ቢሊዮኖን ዶላሮችን ማግኘታቸውን ባሳለፍነው ሳምንት የወጣ ሪፖርት አመላከተ።
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት “ቢግ ቴክ ሴልስ ዋር” የተሰኘ ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ዋ አድርጎ ባወጣው መረጃ፤ ከአውሮፓውያኑ 2004 አንስቶ አማዞን፣ ፌስቡክ፣ ጉግል፣ ማይክሮሶፍት እና ትዊተር በዋናነት በጦርነት ላይ ያተኮሩ ትላልቅ ኮንትራቶችን ከመንግስት ወስደው ሲሰሩ እንደነበር ገልጿል።
የአሜሪካ ጦር ኃይል እና ስለላ ተቋማት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጉዜ ወደ ዲጂታል እየተለወጠ መምጣቱን ተከትሎ በክላውድ ኮምፒውቲንግ እና ጂፒኤስ ሶፍትዌሮች ረገድ ፍላጎታቸውም እየጨመረ ቆይቷል።
የመከላከያ ቢሮውን እንኳን ብናይ ከአውሮፓውያኑ 2004 አንስቶ ከትላልቆቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር ባደረገው ስምምነት 43 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ወጪ ማውጣቱን ሪፖርቱ ያመላክታል።
ከዚህም ባሻገር ከትላልቆቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ገንዘብ ከሚያወጡት መካከል ከፊት የሚቀመጡት አምስቱ ተቋማት ሀገሪቱ ያወጀችው ይህን ዓለም አቀፍ ጦርነት ተከትለው የተመሰረቱ አልያም ከውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር የተሳሰሩ ናቸው።
በቅርቡ አማዞን እና ማይክሮሶፍት የነዚህ ስምምነቶች ቀዳሚ ተጠቃሚ ወደ መሆን የተሸጋገሩ ሲሆን፤ ከ2015 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ አማዞን 5፣ ማይክሮሶፍት ደግሞ 8 ያህል ትላልቅ ኮንትራቶችን ከተቋማቱ መውሰዳቸው ተነግሯል።
ማይክሮሶፍት በተለይ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመን የሚያገኛቸው ከመከላከያ ጋር የተያያዙ መንግስታዊ ኮንትራቶች በይበልጥ አድገውለት እንደነበረም ነው በሪፖርቱ የተመላከተው።
በሌላ መልኩ ግን ለወትሮ የጦር ኃይሉ ደንበኛ የነበሩት የኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የኮንትራት ድርሻ በማሽቆልቆል ላይ መሆኑም ነው የተገለፀው።
መረጃው አሜሪካዊያን መንግስታቸው ውል የሚገባባቸው ኮንትራቶችን እንዲያጋልጡ በሚጠይቅ የበይነ መረብ መንገድ የተወሰዱ መሆናቸውን ቢግ ቴክ ሴልስ ዋር አስታውቋል።
መረጃዎቹን እስካሁን ማግኘት የተቻለው መንግስት ለህዝብ ይፋ ያደረጋቸው ስምምነቶች ብቻ እንደመሆኑ እውነተኛው የኮንትራቶቹ መጠን ከተጠቀሰውም በላይ ላቅ ያለ ሊሆን ይችላም ብሏል ሪፖርቱ።