OMG የተጠቃሚውን መረጃ በመውሰድ ወደ ሌላ ቦታ እንዲያስተላልፍ ተደርጎ የተሰራ ነው ተብሏል
ማርክ ግሪን የተባለ የደህንነት ተመራማሪ OMG የተሰኘው የቻርጀር ገመድ የተጠቃሚውን መረጃ በመውሰድ ወደ ሌላ ቦታ እንዲያስተላልፍ አድርጎ መስራቱ ተነገረ፡፡
ይህም ገመድ በተለይ ሀከሮች (የመረጃ መንታፊዎች) ከተለያዩ ኮምፒውተሮችና የሞባይል ስልኮች ላይ የሚፈልጉትን መረጃ ማስተላለፍ እንዲችሉ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል፡፡
ገመዱ ከተሰካበት ኮምፒውተር ወይም ስልክ ላይ ያሉ የይለፍ ቃላትንና ሌሎች ምስጢራዊ መረጃዎችን ለመመንተፍ ሁነኛ ዘዴ ተደርጎም ተወስዷል፡፡
ከዚህ በፊት የነበረው ላይትኒንግ የተሰኘው ገመድ ስልኮቻችንን ከኮምፒውተር ጋር በማያያዝ ሀይል መሙላት የሚያስችል የነበረ ሲሆን ማርክ ግሪንና ጓደኞቹ ለዚህ ገመድ ማሻሻያ አድርገውለታል፡፡
አሁን ላይ ገመዱ መረጃን አከማችቶ ከመያዝ በተጨማሪ በውስጡ በተገጠመለት የ WiFi ቺፕ አማካኝነት መረጃውን ወደ ሌሎች ቦታዎች ማስተላለፍ ይችላል፡፡
ማርክ ግሪን ይህንን ገመድ በዚህ መልክ ያሻሻለበትን ምንያት ሲናገር በቴክኖሎጂው ዙሪያ ያሉ ሰዎች ይህን ማድረግ አይቻልም የሚል እምነት የነበራችው በመሆኑ፤ በተለይም መረጃን ለማከማቸት እና ለማስተላለፍ የሚረዱ ቁሶችን በገመዱ ውስጥ መግጠም ያስቸግራል ስለሚሉ ይህ እንደሚቻል ለማሳየት እንደሆነ ተናግሯል፡፡
አንድ ሰው ይህን ገመድ በመጠቀም ስልኩን ቻርጅ ሲሞላ ወይም መረጃ ሲያስተላልፍ ገመዱ ስራውን ውስጥ ለውስጥ ይሰራል፡፡ ሀከሮችም ገመዱ የሚሰራውን ስለሚያውቁ ባዘጋጁት የመረጃ ቋት በኩል ሆነው ይጠባበቃሉ፡፡
ይህም የሚያሳየን የምንጠቀማቸውን ኬብሎች ምንነት መለየት እንዳለብን ነው፡፡ በተለይ ከፍተኛ የሆኑ ሀገራዊ ተቋማትና ድርጅቶች ውስጥ የምንጠቀማቸው የኤሌክትሮኒክስ ቁሶች ምንነት በሙያተኛ ተጣርቶ መጠቀም እንደሚገባ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት አሳስቧል፡፡