ኢትዮጵያ ሱዳን በፈጸመችው ወረራ 1 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ጉዳት መድረሱን ገለጸች
ራስን የመከላከል ህጋዊ መብቷን ልትጠቀም እንደምትችል ኢትዮጵያ ፍንጭ ሰጥታለች
ኢትዮጵያ የድንበሩን ድርድር ለመጀመር የሱዳን ን ከያዘችውን ቦታ መልቀቅ እንደቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ችግር በተመለከተ አሁንም በሰላም እና በመነጋገር መፍታት ይቻላል የሚል እምነት እንዳላትና ለዚህም ዝግጁ መሆኗን በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር አስታወቁ፡፡
አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ሱዳን ይህንን ሰላማዊ ጥሪ የማትቀበል ከሆነ ኢትዮጵያ ራስን የመከላከል ሕጋዊ መብቷን ልትጠቀም እንደምትችልም ገልጸዋል፡፡
“ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው ወረራ ታሪካዊ ስህተት ነው” ያሉት ዲፕሎማቱ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው ወረራ ከሞራል፣ ከሕግ ብሎም ሁለቱ ሀገራት ካላቸው የቆየ ወዳጅነት አንጻር ሲታይ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነም ነው ያስታወቁት፡፡
ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መግለጫ የሰጡት አምባሳደሩ ሱዳን እንደ በፈረንጆች አቆጣጠር 1972 በሁለቱ መንግስታት የተደረሰውን የድንበር መርህ በጣሰ መልኩ ወረራ መፈጸሟንና ጉዳት ማድረሷን አስታውቀዋል፡፡
ሱዳን በፈጸመችው ወረራ በንብረት እና በሰው ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን ጉዳቱም በግምት እስከ 1 ቢሊየን ብር የሚጠጋ መሆኑን አምባሳደር ይበልጣል አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል ህግ ለማስከበር በተንቀሳቀሰበት ወቅት የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ሱዳን ወረራ መፈጸሟንና ከጀርባ የመውጋት ድርጊት መፈጸሟን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየገለጸች ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሱዳን ከያዘችው ቦታ ለቃ የድንበር ድርድር እንዲካሄድ እንምትፈልግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ሱዳን ግን ድንበር አለመጣሷንና የያዘችውን ቦታ እንደማትለቅ ገልጻለች፡፡