ቢልጌት ለአፍሪካ 7 ቢሊየን ዶላር መመደቡን ገለጸ
በጀቱ የአፍሪካን ጤና እና ግብርና ስራዎችን ለማዘመን እንደሚውል ተገልጿል
ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌት ፈውንዴሽን የአፍሪካ ቢሮውን በናይሮቢ ለመክፈት መወሰኑን አስታውቋል
ቢልጌት ለአፍሪካ ጤና እና ግብርና ስራዎች ድጋፍ 7 ቢሊየን ዶላር መመደቡን ገለጸ።
የማይክሮሶፍት ኩባንያ መስራች እና የአለማችን ባለጸጋ ቢልጌት ለአፍሪካ ጤና እና ግብርና ስራዎችን ለማዘመን ሰባት ቢሊዮን ዶላር መመደቡን አስታውቋል።
ቢልጌት ከሰሞኑ አፍሪካን የጎበኘ ሲሆን በኬንያ መዲና ናይሮቢ እና ዙሪያው ያሉ የጤና ፣ ግብርና እና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማትን እንደጎበኙ ሮይተርስ ዘግቧል።
ቢልጌት በናይሮቢ ከሚገኙ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ጋርም ቆይታ ያደረጉ ሲሆን ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ፋውንዴሽን ለአፍሪካ በሚያደርገው ድጋፍ ዙሪያ ለተማሪዎቹ ገለጻ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ቢልጌት በዚህ ጊዜ እንዳሉት የአፍሪካ ጤና፣ ግብርና እና ሌሎች አስፈላጊ ስራዎች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው ፋውንዴሽናቸው ሰባት ቢሊዮን ዶላር መመደቡን ጠቅሰዋል።
በጀቱ በቀጣይ አራት ዓመት ለሚከናወኑ የግብርና እና ጤና ስራዎች ማዘመን ላይ እንደሚውልም ተገልጿል።
የጤና መሰረተ ልማት እንዲስተካከሉ፣ አነስተኛ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች የምርት ማሻሻያ ድጋፎችን ማድረግ የዚህ ፕሮግራም አካል ይሆናል ተብሏል።
ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ፋውንዴሽን የምስራቅ አፍሪካ ቢሮውን በናይሮቢ ለመክፈት መወሰኑም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።