ቢሊየነሩ ቢል ጌትስ ለበጎ አድራጎት ስራዎች እስካሁን ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ መለገሱ ተነገረ
ቢሊየነሩ እስካሁን ለተለያዩ ድጋፎች ያዋለው ገንዘብ ከቴስላ አመታዊ ሽያጭ ጋር የሚስተካከል ነው
ቢል ጌትስ በቀጣይ ለድህነት ቅነሳ እና ለበሽታ መከላከል ተጨማሪ ቢሊየን ዶላሮችን ድጋፍ የማድረግ እቅድ አለኝ ብሏል
የታዋቂው የማይክሮሶፍት ኩባንያ ባለቤት እና ቢሊየነሩ ቢል ጌትስ በበጎ አድራጎት ድርጅት ፋውንዴሽኑ በሽታዎችን ለመከላከል እና ድህነትን ለመቀነስ በሚያደርገው ጥረት ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጣ አዲስ ቁጥሮችን ይፋ አድርጓል።
ባለሀብቱ እስካሁን የተለያዩ አይነት የበጎአድራጎት ስራዎችን ለመደገፍ ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ ማውጣቱን ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡
ይህም ከቡልጋሪያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ እና ከኢለን መስክ ቴስላ አመታዊ ሽያጭ ጋር የሚስተካከል መሆኑ ተሰምቷል፡፡
መልካም ነገርን ማድረግ ከእናቱ የተማረው እንደሆነ የሚናገረው ቢልጌትስ ከሌላኛው በጎ አድራጊ ባለሀብት ዋረን ቡፌት ጋር በመሆን በቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽ በኩል በርካታ ድጋፎችን ማድረጉን ገልጿል፡፡
በተጨማሪም የፋውንዴሽኑ 25ኛ አመት በሚከበርበት ጊዜ ተጨማሪ 100 ቢሊየን ዶላር የድጋፍ እቅድ ይፋ ለማድረግ መዘጋጀቱን ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡
በፈረንጆቹ 2000 የተመሰረተው ተቋም በመጪው ግንቦት ወር 25ኛ አመቱን የሚያከብር ሲሆን ከሁለት አስርተ አመታት ለሚሆኑ ጊዜያት በ135 ሀገራት ለተለያዩ የእርዳታ ፕሮግራሞች ድጋፍ አድርጓል፡፡
ፋውንዴሽኑ በዋናናት ድህነትን መቀነስ፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማሻሻል፣ የትምህርት እና የመረጃ ቴክኖሎጂ አገልግሎትን ማስፋት፣ ተላላፊ በሽታዎችን ማጥፋት እና የንፅህና አጠባበቅን ማሻሻል ላይ አተኩሮ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ከአሜሪካ በመቀጠልም ለአለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ገንዘብ በመለገስ የቢል እና ሚሊንዳጌትስ ፋውንዴሽን በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከዋረን ቡፌት ጋር በመሆን ሌሎች ቢሊየነሮች እና ባለሀብቶች ለበጎ አድራጎት እንዲለግሱ ለማበረታታት "የመስጠት ቃል ኪዳን" የተሰኝ ስርአት መስርተዋል።
የሀብቱን በርካታ ክፍል ለበጎ አድራጎት ስራ መድቦ የማለፍ እቅድ እንዳለው የሚገልጸው ባለሀብቱ ከሶስት ልጆቹ ጋር በመሆን ምን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ ለእርዳታ መተላለፍ እንዳለበት በመመካከር ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገረው፡፡
ብሉምበርግ ባወጣው ሪፖርት መሰረት ቢልጌትስ አለማችን ላይ ካሉ 100 ቢሊየንን ከተሻገሩ 15 ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ያለው ሀብት 160 ቢሊየን ዶላር ይጠጋል፡፡