የማርከስ ራሽፎርድ የአስቶንቪላ የውሰት ዝውውር ተጠናቀቀ
ከአዲሱ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ጋር መግባባት ያልቻለው የ27 አመቱ አጥቂ እስከ ውድድሩ ዘመን መቋጫ ድረስ በውሰት ይቆያል
በስምምነቱ መሰረት አስቶንቪላ የራሽፎርድን 75 በመቶ ደመወዝ ይከፍላል
አስቶንቪላ የማንቸስተር ዩናይትዱን አጥቂ ማርከስ ራሽፎርድን በውሰት ማስፈረሙ ተገለጸ።
የ27 አመቱ ተጫዋች እስከ የውድድር አመቱ መጨረሻ ድረስ ክለቡን ተቀላቅሏል።
ይህም የመግዛት አማራጭን ያካተተ ነው፡፡
ራሽፎርድ ከስምምነቱ መጠናቀቅ በኋላ በኢንስታግራም ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ ይህ የውሰት ስምምነት እንዲፈፀም በማድረጋቸው ማንቸስተር ዩናይትድን እና አስቶንቪላን አመስግኗል፡፡
“ጥቂት ክለቦች እኔን ፈልገው በመምጣታቸው እድለኛ ነበርኩ ግን አስቶንቪላን መምረጥ ቀላል ውሳኔ ነበር ፤ በዚህ የውድድር ዘመን አስቶንቪላ እየተጫወተ ያለበትን መንገድ እና የአሰልጣኙን ምኞት አደንቃለሁ፤ እግር ኳስ መጫወት ብቻ ነው የምፈልገው እናም ለመጀመር ጓጉቻለሁ” ብሏል፡፡
የዩናይትድ ምንጮችን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው አስቶንቪላ ለማችስተር ለዝውውር ምንም አይነት ክፍያ ያልከፈለ ሲሆን ነገር ግን በክለቡ በሚኖረው ቆይታ 75 የራሽፎርድን ደሞዝ ለመክፈል ተስማምቷል፡፡
በታህሳስ ወር ከማንቸስተር ደርቢ ጨዋታ ከተገለለ በኋላ እንግሊዛዊው ወጣት አጥቂ ራሽፎርድ “ለአዲስ ፈተና ዝግጁ ነኝ” ሲል ከዩናይትድ መልቀቅ እንደሚፈልግ ፍንጭ ሰጥቷል።
ተጫዋቹ በኦልትራፎርድ በነበረው ቆይታ 426 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 138 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን ከቡድኑ ጋር አምስት የተለያዩ ዋንጫዎችን ማሳካት ችሏል፡፡
አዲሱ የቡድኑ አለቃ ፖርቹጋላዊው ሩብን አሞሪም በራሽፎርድ ተነሳሽነት እና ጨዋታን ለማሸነፍ ባለው ቁርጠኝነት ላይ ጥርጣሬ ገብቶኛል በሚል ምክንያት ተጫዋቾችን በተለያዩ ጨዋታዎች ላይ ገሸሽ አድርገውት ቆይተዋል፡፡
እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ራሽፎርድ ራሱን የሚያሻሻል ከሆነ ብቃቱን ለክለቡ እንደሚጠቅም አሰልጣኙ ሲናገሩ ቢቆይም የውስጥ ምንጮች አሞሪም ራሽፎርድ በዩናይትድ እንደማይቆይ ከወሰኑ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሁለቱ ወገኖች ችግሮቻቸውን ፈተው ራሽፎርድ በዩናይትድ እንደሚቆይ ጭላንጭል ተስፋ የነበረ ቢሆን አሁን የተሰማው የውሰት ውል መጠናቀቅ ለጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል ብሏል ቢቢሲ፡፡
አስቶንቪላ ከራሽፎርድ በተጨማሪ ስፔናዊውን አማካኝ ማርኮ አሴንሲዮን ከፒኤስጂ በውሰት ለማስፈረም ተቃርቧል።
ቅዳሜ እለት የቪላ አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሪ ክለቡ በወራጅ ቀጠና በሚገኘው ዎልቭስ 2-0 መሸነፉን ተከትሎ አዳዲስ ተጫዋቾች ያስፈልጉናል ብለዋል።
ስፔናዊውን ተከላካይ አንድሬስ ጋርሺያን ከሌቫንቴ እና ኔዘርላንዳዊውን አጥቂ ዶኔል ማሌንን ከቦሩሲያ ዶርትመንድ በጥር ወር አስፈርመዋል።
ነገር ግን ቪላ ኮሎምቢያዊውን አጥቂ ጆን ዱራንን ለሳውዲ ፕሮ ሊግ ክለብ አል ናስር በ71ሚሊየን ፓውንድ እና የመሀል ተከላካዩን ዲያጎ ካርሎስን ለፌነርባቼ በ8.45 ሚሊየን ፓውንድ ሸጧል።