ፑቲን ሶቬየት የናዚ መግደያ ካምፖችን ነጻ በማድረግ የነበራትን ሚና መካድ አሳፋሪ ነው አሉ
በፖላንድ የሚገኘው የናዚ መግደያ ካምፕ ኦሽዊዝ ካምፕ በሶቬት ወታደሮች ነጻ የወጣበት 80ኛ አመት ተዘክሯል
የጀርመኑ ናዚና ተባባራዎቹ ከ1941 እስከ 1945 ድረስ ጀርመን በተቆጣጠረችው የአውሮፓ ክፍል 6 ሚሊዮን አይሁዶችን ስልታዊ በሆነ መንገድ ገድሏል
ፑቲን ሶቬየት የናዚ መግደያ ካምፖችን ነጻ በማድረግ የነበራትን ሚና መካድ አሳፋሪ ነው አሉ።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሶቬት ህብረት እንደ ኦሽዊትዝ የመሳሰሉ የናዚ መግደያ ከምፖችን ነጻ በማድረግ የነበራትን ሚናና ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ቤተሰቦችን በነጻነት መታቢያ ቀን አለመጋበዝ አሳፋሪ ነው ብለዋል።
በፖላንድ የሚገኘው የኦሽዊዝ ካምፕ በሶቬት ወታደሮች ነጻ የወጣበት 80ኛ አመት የጀርመን መሪ ኦላፍ ሾልዝ፣የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ፣ የብሪታኒያው ንጉስ ቻርለስ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የፖላንዱ ፕሬዝደንት አንድሬዜጅ ዱዳና ልሎች መሪዎች በተገኙበት ተዘክሯል።
አብዛኛውን የሶቬት ግዛት የያዘችው የዛሬዋ ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደች ባለው ጦርነት ምክንያት አልተጋበዘችም።
"ይህ እንግዳና አሳፋሪ ተግባር ነው" ሲሉ ፑቲን ዛሬ በተለቀቀው ከመንግስት ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
"የሩሲያን መሪ በፈለጋችሁ መልኩ ልታዩ ትችላላችሁ፤ ማንም ግብዣ አልጠየቀም። ነገርግን አስባችሁበት ቢሆን ኖሮ ሌሎች መንገዶች ነበሩ።"
ፕሬዝደንት ፑቲን በእድሜ መግፋትና በጤና ምክንያት ካምፖቹን ነጻ በማውጣት ሂደት የተሳተፉ የሶቬት ወታደሮች ሊጋበዙ ባይችሉም፣ ቤተሰቦቻቸውን በነጻነት ማስታወሻው ቀን ላይ መጋበዝ ይችሉ ነበር ብለዋል።
የሶቬት ህብረት ወታደሮች በ1944 እና በ1945 የናዚ ወታደሮችን ወደ ኋላ ከገፉ በኋላ ማድዳኔክ፣ ኦሽዊትዝ፣ስቱትሆፍ፣ ሳቸሰንሀውሰንና ራቤንስብረክን ጨምሮ በርካታ የናዚ መግደያ ካምፖችን ነጻ አድርገዋል።
የአሜሪካና የእንግሊዝ ጦሮችም ሌሎች ከምፖችን ነጻ አድርገዋል። በአብዛኛው አይሁድ የነበሩ ከ1.1ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኦሾዊትዝ በመርዝ ጋዝ፣ በረሃብ እና በበሽታ ሞተዋል።
ከአይሁዶች ቀጥሎ ፖሎች፣ ሮማ፣ ሲንቲና የሶቭየት የጦር እስረኞች የግድያ ሰለባው እንደነበሩ የኦሽዊትዝ መረጃ ያመለክታል።
የጀርመኑ ናዚና ተባባራዎቹ ከ1941 እስከ 1945 ድረስ ጀርመን በተቆጣጠረችው የአውሮፓ ክፍል 6 ሚሊዮን አይሁዶችን ስልታዊ በሆነ መንገድ ገድሏል። ከአይሁዶች ቀጥሎ በከፍተኛ ቁጥር የተገደሉት የሶቬየት የጦር እስረኞች ነበሩ።