ተቀጣሪ ሰራተኞች ከቢሊየነሮች በላይ ለመንግስት ግብር ይከፍላሉ ተባለ
ቢሊየነሮች የአለማችን ከግማሽ በላይ ሃብት ቢቆጣጠሩም ግብር አይከፍሉም ማለት ይቀላል ብሏል በፓሪስ ይፋ የተደረገ ጥናት
በቢሊየነሮች ላይ የሚጣለው ግብር በአግባቡ ቢሰበሰብ በአመቱ በጥቂቱ 250 ቢሊየን ዶላር ማግኘት እንደሚቻል ጥናት አመላክቷል
የአለም መንግስታት ግብርን በሚሰውሩ ቢሊየነሮች ላይ አዲስ ዘመቻ ሊከፍቱ እንደሚገባ ተገለጸ።
ተቀማጭነቱን ፓሪስ ያደረገው የአውሮፓ ታክስ ኦብዞርቫቶሪ ያወጣው ሪፖርት እንዳመላከተው የአለማችን ቢሊየነሮች የሚከፍሉት የገቢ ግብር ከተቀጣሪ ሰራተኞች ጋር ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም።
የአሜሪካ ቢሊየነሮች የሚከፍሉት የገቢ ግብር 0 ነጥብ 5 ገደማ ነው፤ በፈረንሳይ ደግም ምንም አይከፍሉም ማለት ይቻላል ብሏል ሪፖርቱ።
በአለም ዙሪያ ያሉ 2 ሺህ 700 ቢሊየነሮች 13 ትሪሊየን ዶላር የሚጠጋ ሀብት ቢኖራቸውም በወረቀት ላይ ብቻ ያሉ ኩባንያዎቻቸው (ሼል ካምፓኒ) አማካኝነት ግብር በመሰወር በየአመቱ ሊከፍሉት የሚገባ ግብርን ያመልጣሉ።
ቢሊየነሮቹ ትርፋቸውን አነስተኛ ግብር በሚጣልባቸው ሀገራት እንዲመዘገብ ማድረጋቸውም ሌላኛው የማምለጫ መንገዳቸው ነው ይላል ጥናቱ።
ይህን የታክስ ስወራ ለመከላከልም 140 ሀገራት በ2021 በቢሊየነሮች ኩባንያዎች ላይ የሚጣለው ዝቅተኛ ግብር 15 በመቶ እንዲሆን ቢስማሙም ተፈጻሚ ለማድረግ አዳጋች ሆኗል።
ከአሜሪካ ህዝብ 1 በመቶ የሚሆኑት ቢሊየነሮች ላይ የሚጣለውን ግብር በ25 በመቶ ለማሳደግ የጆ ባይደን አስተዳደር እቅድ ቢይዝም በኮንግረንሱ ግን ይጸድቃል ተብሎ አይጠበቅም።
በአለማቀፍ ደረጃ እየሰፋ የመጣውን የሃብት ልዩነት ለማጥበብ ቢሊየነሮች ላይ የሚጣለው ግብር ማደግ እንዳለበት የሚጠቅሰው የአውሮፓ ህብረት የታክስ ኦብዞርቫቶሪ ተቋም፥ በአጭር ጊዜ ለውጥ ለማየት አዳጋች መሆኑን ያብራራል።
ይሁን እንጂ በ2021 በተደረሰው ስምምነት እንኳን ግብር ቢከፍሉ በየአመቱ ተጨማሪ 250 ቢሊየን ዶላር ማግኘት እንደሚቻልና ይህም ከቢሊየነሮቹ ጠቅላላ ሃብት 2 ከመቶ ብቻ መሆኑንም ይጠቅሳል።
ከቢሊየነሮች ሃብት እና ትርፍ ጋር በተያያዘ በባንኮች የሚያዙ ሚስጢሮች መላላት ካልጀመሩና ቢሊየነሮች ትርፋቸውን አነስተኛ ግብር ወደሚጣልባቸው ሀገራት ማሸሻቸውን ከቀጠሉ ግን የግብር ስወራው ይቀጥላልም ነው ያለው ሪፖርቱ።
ሀገራት ከ2018 ጀምሮ የባለሃብቶችን የባንክ ሂሳብ መረጃ ለመለዋወጥ መስማማታቸው ያስገኘውን ውጤት በማውሳትም የሀገራት የተቀናጀ ዘመቻ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ገልጿል።
ከአለማችን ህዝብ 1 በመቶ የሚሆኑት ባለጠጎች የምድራችን ከግማሽ በላይ ሃብት ተቆጣጥረዋል፡፡
ኦክስፋም በ2020 ያወጣው ሪፖርት እንዳመላከተው 2 ሺህ 134 ቢሊየነሮች ከአለማችን 60 በመቶ ህዝብ (4 ነጥብ 6 ቢሊየን) የተሻለ ሃብት አካብተዋል።
የአለም ኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካ የሚዘወረውም በነዚህ 1 በመቶዎቹ በመሆኑ ከተቀጣሪ ሰራተኞች ያነሰ ግብር ለመክፈል ባለመፍቀድ ግብር በመሰወር ላይ ሲጠመዱ ብዙዎች አይተው እንዳላዩ ያልፏቸዋል።