ሁሉም ከተሞች የሚታወቁባቸው የየራሳቸው መልካም እና መጥፎ ሁኔታዎች አሏቸው
ሁሉም ከተሞች የሚታወቁባቸው የየራሳቸው መልካም እና መጥፎ ሁኔታዎች አሏቸው።
በተለይም ባለጸጋዎች ለስራቸው እና ለህይወታቸው የሚስሟሟቸውን ከተሞች በጥንቃቄ የሚመርጡ ሲሆን ተመራጭ ከተሞችን እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።
ከዓለማችን ቢሊየነሮች ውስጥ 543ቱ የሚኖሩት በ20 ከተሞች ውስጥ ሲሆን የአሜሪካዋ ኒዮርክ 340 ሺህ ሚሊየነሮች እና 59 ቢሊየነሮች መኖሪያ በመሆን ቀዳሚ ተመራጭ ከተማ ተብላለች።
የጃፓኗ መዲና ቶኪዮ ደግሞ 305 ሺህ ሚሊየነሮች እና 12 ቢሊየነሮች ይኖሩባታል።
ሌላኛዋ የአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ከተማ 276 ሺህ ሚሊየነሮች እና 26 ቢሊየነሮችን በማኖር ሶስተኛዋ የባለጸጋዎች መኖሪያ ከተማ ናት።
የእንግሊዝ መዲና የሆነችው ለንደን ከተማ አራተኛዋ የዓለማችን ባለጸጋዎች መኖሪያ ስትሆን 272 ሺህ 400 ሚሊየነሮች እና 38 ቢሊየነሮች ይኖሩባታል።
ከእስያ አህጉር ደግሞ ቀዳሚዋ የባለጸጋዎች መኖሪያ ምርጫ የሆነችው ሲንጋፖር ስትሆን 250 ሺህ ሚሊየነሮች እና 62 ቢሊየነሮች ይኖሩባታል።
ሌላኛዋ የአሜሪካ ከተማ በሆነችው ሎስ አንጀለስ ደግሞ 192 ሺህ ሚሊየነሮች እና 34 ቢሊየነሮች እንደሚኖሩባት ተገልጿል።
እንዲሁም በቺካጎ ደግሞ 160 ሚሊየነሮች እና 28 ቢሊየነሮችን ታኖራለች።
የዓለማችን ሁለተኛዋ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ሀገር የሆነችው የቻይና መዲና ቤጂንግ ደግሞ 131 ሺህ ሚሊየነሮች እና 44 ቢሊየነሮች ይኖሩባታል ተብሏል።
ሌላኛዋ የቻይና የቴክኖሎጂ ከተማ በሆነችው ሻንጋይ ከተማ ደግሞ 130 ሺህ ሚሊየነሮች እና 42 ቢሊየነሮች እንደሚኖሩባት ተገልጿል።
የአውስትራሊያዋ ሲድኒ ደግሞ 129 ሺህ ሚሊየነሮች እና 16 ቢሊየነሮች እንዲሁም ሆንግ ኮንግ 125 ሚሊየነሮች እና 28 ቢሊየነሮች ይኖሩባቸዋል ተብሏል።
የጀርመኗ ፍራንክፈርት ደግሞ ከአውሮፓ ከተሞች ውስጥ በባለጸጋዎች የምትወደድ ከተማ ስትሆን 117 ሺህ ሚሊየነሮች እና 17 ቢሊየነሮች እንዲሁም ዙሪክ ከተማ ደግሞ 105 ሚሊየነሮች እና 12 ቢሊየነሮች ይኖሩባቸዋል።
የደቡብ ኮሪያ መዲና ሲኡል፣ ሜልቦርን፣ ጀኔቫ እና ፓሪስ ከተሞች በተጨማሪነት የዓለማችን ባለጸጋዎች ለኑሯቸው እና ስራቸው የሚመርጧቸው ከተሞች እንደሆኑ ተገልጿል።
ኒዮርክ ከተማ በአጠቃላይ ሶስት ትሪሊዮን ዶላር ሀብት ያላቸው ባለጸጋዎች የሚኖሩባት ሲሆን ቶኪዮን በአክስዮን እና ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰማሩ የዓለማችን ባለጸጋዎች ይመርጧታል።