በ2024 በየሳምንቱ አራት ቢሊየነሮች የባለጸጎችን ዝርዝር ተቀላቅለዋል- ኦክስፋም
በቀጣይ አስር አመታት ውስጥም አምስት ትሪሊየነሮች እንደሚፈጠሩና የአለማችን የሀብት ልዩነት እየሰፋ እንደሚሄድ ነው ኦክስፋም ያስታወቀው
የአለም የኢኮኖሚ ፎረም በስዊዘርላንድ ዳቮስ መካሄድ ጀምሯል
በ2024 የአለማችን ቢሊየነሮች የሃብት እድገት ከ2023ቱ በሶስት እጥፍ ፈጣን እንደነበር ኦክስፋም ኢንተርናሽናል ገለጸ።
ኦክስፋም የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ከመጀመሩ አስቀድሞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በቀጣይ አስር አመት በጥቂቱ አምስት ትሪሊየነሮች ይፈጠራሉ ብሏል።
ከአንድ አመት በፊት በአስር አመት ውስጥ አለማችን አንድ ትሪሊየነር ይኖራታል የሚል ሪፖርት ያወጣው ኦክስፋም የባለጠጎችና ድሃዎች የሃብት ልዩነት እየሰፋ ቢሊየነሮች በሀብት ላይ ሀብት እየጨመሩ መሆኑን የሚያመላክት ጥናት ይፋ አድርጓል።
የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ዛሬ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከመጀመሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የወጣው የኦክስፋም ጥናት "ሀብት ፈጣሪዎች ሳይሆኑ ቀማኞች" የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል።
የኦክስፋም ዋና ዳይሬክተር አሚታብ በሃር ትናንት ቃለ መሃላ የፈጸሙት ዶናልድ ትራምፕ በአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ድጋፍ ተችሯቸው ወደ ነጩ ቤተመንግስት ዳግም መግባታቸውን አንስተዋል።
"ይህ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ አይደለም፤ የኢኮኖሚ ስርአቱ ቢሊየነሮች የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፖሊሲዎችን ቅርጽ እንዲወስኑ የሚፈቅድ ነው፤ ይህም በትርፍ ላይ ትርፍ እንዲደርቡ አድርጓቸዋል" ነው ያሉት።
ኦክስፋም የአለም ሀገራት በሀብታሞች ላይ ከፍ ያለ ግብር በመጣል እየሰፋ የሚሄደውን የሀብት ልዩነት ለማጥበብ ሊሰሩ ይገባል ብሏል።
በ2024 የቢሊየነሮች የሀብት መጠን በ2 ትሪሊየን ጨምሮ 15 ትሪሊየን ዶላር ደርሷል፤ የቢሊየነሮቹ ሀብት በየቀኑ በ5 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ይጨምራል።
የአለማችን 10 ቀዳሚ ቢሊየነሮች ሀብት በ2024 በየቀኑ በአማካይ በ100 ሚሊየን ዶላር መጨመሩንም ነው ኦክስፋም የጠቆመው።
ባለፈው የፈረንጆቹ አመት በሳምንት ውስጥ ቢያንስ አራት ቢሊየነሮች የባለጠጎችን ዝርዝር የሚቀላቀሉ ሲሆን፥ የቢሊየነሮች ቁጥር በ204 ጨምሮ 2 ሺህ 769 ደርሷል።
በአንጻሩ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ከብሄራዊ በጀታቸው ግማሽ የሚጠጋውን እዳ ለመክፈል ያውሉታል። ጦርነት እና ግጭቶችን የሚያስተናግዱ ሀገራትም ለጦር መሳሪያ የሚያውሉት ገንዘብ እያደገ የዜጎቻቸውን መሰረታዊ ፍላጎት መመለስ እየተሳናቸው ነው። ጦርነትን እንጀራ ያደረጉ ባለጠጎች በአንጻሩ ገቢያቸው እየተመነደገላቸው ሄዷል።
ከ3 ሽህ በላይ የቢዝነስ ተቋማት መሪዎች፣ ምሁራን፣ የመንግስት ባለስልጣናት እና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች የሚሳተፉበት ጉባኤ በየጊዜው እየሰፋ በሄደው የሃብት ኢፍትሃዊነት ላይ ይመክራል ተብሏል።
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቅርቡ "ስልጣን በጥቂት የናጠጡ ሃብታሞች እጅ ገብታለች" በሚል ያሰሙት ንግግር ከኦክስፋም ሪፖርት ጋር የሚጣጣም ሆኗል።
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው በዳቮስ ሁለት ጊዜ የተገኙት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዘንድሮው ጉባኤ በቪዲዮ እንደሚሳተፉ ፍራንስ 24 ዘግቧል።