ቲክቶክ ለአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ሊሸጥ ነው መባሉን "ልቦለድ" ነው ሲል አስተባበለ
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድቤት ቲክቶክን ለማገድ አምስት ቀናት ብቻ ቀርተውታል
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቲክቶክን ከመዝጋት ይልቅ በፖለቲካዊ ንግግር መፍትሄ መፈለግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል
የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቲክቶክ በአሜሪካ ያለውን ድርሻ በአለማችን ቁጥር አንድ ባለሃብት ኤለን መስክ እንዲተዳደር ተስማምቷል በሚል የወጣውን ዘገባ አስተባበለ።
ብሉምበርግ የቻይና ባለስልጣናት የቲክቶክ ኩባንያ የአሜሪካ ኦፕሬሽን ለኤለን መስክ እንዲሸጥ ጫና እያደረጉ ነው የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር።
ቲክቶክ በአሜሪካ ስራውን ለመቀጠል ለአሜሪካ ኩባንያዎች መሸጥ እንዳለበት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መወሰናቸው ይታወሳል።
የቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያው ግን የአሜሪካ ገበያውን ለአሜሪካ ባለሀብቶች እንደማይሸጥ በተደጋጋሚ ገልጿል።
ብሉምበርግ ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው የኤለን መስኩ ኤክስ የቲክቶክን የአሜሪካ ድርሻ ገዝቶ እንዲቆጣጠር እንደ አንድ አማራጭ ቀርቧል። ይሁን እንጂ ኤክስ ስለጉዳዩ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም።
የቲክቶክ ቃልአቀባይ በበኩላቸው "ግልጽ ለሆነ ልቦለድ ምላሽ መስጠት አይጠበቅምብንም" በሚል የብሉምበርግን ዘገባ ውድቅ አድርገዋል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቲክቶክ በአሜሪካ እንዲዘጋ ከአምስት ቀናት በኋላ የመጨረሻ ውሳኔውን ያሳልፋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ፍርድቤቱ አከራካሪውን ውሳኔ የሚያሳልፈው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ዋይትሃውስ ከመግባታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።
ትራምፕ ጠቅላይ ፍርድቤቱ ውሳኔ ለማሳለፍ የያዘውን ቀጠሮ እንዲያራዝመውና "ፖለቲካዊ መፍትሄ" ለመፈለግ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቲክቶክን የተጠቀሙበት ትራምፕ ለበርካታ አሜሪካውያን የስራ እድል የፈጠረው ቲክቶክ እንዲዘጋ እንደማይፈልጉ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ትራምፕ በፍሎሪዳ ማርላጎ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሹ ዚ ቸው ጋር መምከራቸውም የሚታወስ ነው።
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ቲክቶክ ለአሜሪካ ባለሀብቶች ካልተሸጠ የቻይና የስለላ ስራ ማቀላጠፊያ ሆኖ ይቀጥላል የሚል ስጋት አላቸው።
ቲክቶክ ግን ኩባንያው ከቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ምንም አይነት ጫና እንደማይደረግበትና የተጠቃሚዎቹን መረጃ አሳልፎ እንደማይሰጥ በተደጋጋሚ መግለጹ አይዘነጋም።