ቬትናማዊቷ ቢሊየነር ከሞት ለማምለጥ 9 ቢሊየን ዶላር በማሰባሰብ ተጠምደዋል ተባለ
ከ12 ቢሊየን ዶላር በላይ በመዝረፍ የሞት ቅጣት የተላለፈባቸው ትሩኦንግ ማይ ላን ያቀረቡት ይግባኝ ውድቅ ተደርጎባቸዋል
ቢሊየነሯ እንዳሻቸው ሲያደርጉት ከነበረው “ሳይጎን” ባንክ 44 ቢሊየን ዶላር ብድር በማጭበርበር ወስደዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር
የቬትናም ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር ትሩኦንግ ማይ ላን የሞት ፍርድ እንዲነሳላቸው ያቀረቡት ይግባኝ ውድቅ ተደረገ።
በአለማችን ትልቁን የባንክ ማጭበርበር ፈጽመዋል የተባሉት ትሩኦንግ በአሁኑ ወቅት ህይወታቸውን ለማትረፍ 9 ቢሊየን ዶላር በማፈላለግ ተጠምደዋል ተብሏል።
ቢሊየነሯ መዝብራዋለች ከተባለው ገንዘብ ውስጥ 75 በመቶውን ከመለሰች ቅጣቱ ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲለወጥላት የሀገሪቱ ህግ ይፈቅዳል።
በሆቺ ሚኒ ከተማ የሚገኘው ፍርድ ቤት ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር ላይ ነበር ሳይጎን የተሰኘውን የሀገሪቱን ባንክ እንዳሻቸው በመዘወር ለ11 አመታት ግዙፍ የማጭበርበርና ዝርፊያ ወንጀል ፈጽመዋል ባላቸው የ68 አመት አዛውንት ላይ የሞት ቅጣት ያሳለፈው።
ቢሊየነሯ በበርካታ ሚስጢራዊ ኩባንያዎቻቸው ከ44 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር በማጭበርበር መውሰዳቸውንና 12.5 ቢሊየን ዶላር መዝረፋቸውን ክሱ ያመላክታል።
የሞት ፍርዱ ቢሊየነሯ በተለያዩ ሚስጢራዊ ኩባንያዎቻቸው የደበቁትን ሀብት በመጠቀም ብድራቸውን እንዲመልሱ ያበረታታል ተብሎ ታምኖበታል።
የቢሊየነሯ ጠበቆች በሆቺ ሚኒ ከተማ የሚገኙት ውድ ሃብቶቻቸውን ለመሸጥ ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም አክሲዮኖች እና ሌሎች ንብረቶችን በመሸጥ 9 ቢሊየን ዶላሩን ለማሟላት ጥድፊያ ላይ ናቸው ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
ከግዙፉ የባንክ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በሺዎች የሚቆጠሩ ሃብቶች እንዳይንቀሳቀሱ በፍርድ ቤት መታገዳቸውም ከሞት ማስመለጫውን ማሰባሰብ ፈታኝ ያደርገዋል ተብሏል።
የትሩኦንግ ማይ ላን የሃብት ጉዞ እና ሳይጎን ባንክ
ሁሉም መሬት በመንግስት በሚተዳደርባት ቬትናም ለሆቴልም ሆነ ለፋብሪካ መሬት ለማግኘት ከባለስልጣናት ጋር ልዩ ግንኙነት መመስረት ግድ ነበር። ይህም እድገቷ ፈጣን የነበረውን ሀገር ሙስና እንዲስፋፋባት አድርጓል።
ሁኔታው የሀገሪቱ መንግስት በፈረንጆቹ 1986 የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲያደርግ ሲያስገድደው የመዋቢያ እቃዎችን በመሸጥ የንግዱን አለም የተቀላቀሉት ትሩኦንግ ማይ ላን መሬት በስፋት መግዛት ጀመሩ።
በሆቺ ሚኒ የታዋቂ ሁቴሎች ባለቤት መሆን የቻሉት ትሩኦንግ ሀብት በሀብት እየደረቡ ሲሄዱም ጊዜ አልወሰደባቸውም።
የሳይጎን ንግድ ባንክ ግን ዋነኛ መወጣጫቸው ነበር ይላል የቀረበባቸው ክስ።
የቬትናም ህግ ማንኛውም ግለሰብ በየትኛውም ባንክ ውስጥ ከ5 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳይኖረው ቢከለክልም ቢሊየነሯ ግን በኩባንያዎቻቸው ስም ባንኩን የግል ንብረታቸው አድርገውታል ነው የተባለው።
የባንኩን ስራ አስኪያጆች እንዳሻቸው እየሾሙ ስም እንጂ ሰራተኛም ሆነ ስራ ለሌላቸው “ሼል ኩባንያዎች” በቢሊየን ዶላር ብድር እንዲፈቅዱ ሲያደርጉ እንደነበር ክሱ ያስረዳል። ባንኩ ከለቀቀው ብድር ውስጥ 93 በመቶው ለትሩኦንግ ማይ ላን ኩባንያዎች የቀረበ እንደነበርም ተገልጿል።
ከ2019 ጀምሮ ለሶስት ዓመታት ሾፌራቸው 108 ትሪሊየን የቬትናም ዶንግ (ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ) በጥሬ ገንዘብ እንዲያወጣ አድርገው በምድር ቤታቸው ማከማቸታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ የተከማቸው የገንዘብ ኖት ሁለት ኩንታል ይመዝናል መባሉም አነጋጋሪ ነበር።
የቬትናም ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ንጉየን ትሮንግ ሙስና የፓርቲያችን ህልውና አደጋ ነው ብለው በ2016 የጀመሩት ዘመቻ ሁለት ፕሬዝዳንቶች እና ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ከስልጣን እንዲለቁ አድርጎ ትሩኦንግ ማይ ላንንም ዘብጥያ ወርውሯል።
2 ሺህ 700 ምስክሮችና ከ5 ሺህ 400 ኪሎግራም በላይ የሚመዝኑ ማስረጃዎች የቀረቡባቸው ቢሊየነሯ ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር የሞት ቅጣት ተላልፎባቸዋል።