10 ሺህ ሲኒ ቡና የተጠጣበት “ታላቁ የቡና ቅመሱ ስነ ስርዓት” አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዘገበ
የቡና ቅመሱ ስነ ስርዓቱ ባሳለፍነው አርብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል
የቡና ስነ ስርዓት ለማዘጋጀት 100 ኪሎ ግራም ቡና፣ 10 ሺህ ሲኒዎችና 100 ጀበናዎች ጥቅም ላይ ውለዋል
በአዲስ አበባ የተካሄደውእና 10 ሺህ ሲኒ ቡና የተጠጣበት “ታላቁ የቡና ቅመሱ ስነ ስርዓት” አዲስ ክብረወሰን ሆኖ መመዝገቡ ተገለፀ።
“ታላቁ የቡና ቅመሱ ስነ ስርዓት” ባሳለፍነው አርብ በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በሚገኘው የኦሮሞ ባህል ማእከል ተካሂዷል።
በዚህ ስነ ስርዓት ላይም 10 ሺህ ሲኒ ቡና ለታዳሚዎች መቅረቡን ከኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ስነ ስርዓቱን ለማዘጋጀት 100 ኪሎ ግራም ቡና ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፤ 10 ሺህ የቡና መጠጫ ሲኒዎች እና 100 ጀበናዎችን መጠቀማቸውንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ቡናው የቀረበበት ረከቦትም 35 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ 5 ሜትር ስፋት እና 65 ሴንቲ ሜትር ከፍታ ያለው መሆኑም ተገልጿል።
የቡና ማቅረቡያ ረከቦቱ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የእንጨት ስራ ኢንተርፕራዝ የተሰራ ሲሆን፤ አጠቃላይ “የታላቁ የቡና ቅመሱ ስነ ስርዓት” ፕሮጀክት ሶስት ሳምንተትን የፈጀ መሆኑንም የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን አስታውቋል።
ይህ “ታላቁ የቡና ቅመሱ ስነ ስርዓት” መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ድንቃድንቅ መዝገብ በተባለ ድርጅት “በአይነቱ ግዙፍ የሆነ እና አዲስ የቡና ጠጡ ክብረ ወሰን” አድርጎ መዝግቦታል።
የቡና ስነ ስርዓቱ አዲስ ክብረወሰን መሆኑን የሚያረጋግጥ የምስርክር ወረቀትም ከአፍሪካ ድንቃድንቅ መዝገብ ለኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ተበርክቷል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ባሳለፍነው ሳምንት ለኢሬች በዓል መዳረሻ የተለያዩ ስነ ስርዓቶችን ማዘጋጀቱ ይታወሳል።
ከተካሄዱ ስነ ስርዓቶች ውስጥም “የሚስ ቱሪዝም ኦሮሚያ” የቁንጅና ውድድር እና የቱሪዝም ሽልማት ይገኝበታል።